
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በእስልምና አስተምህሮ መሠረት ጾም እና ዘካ ተደጋጋፊ እና ተመጋጋቢ የእምነቱ ምሰሶዎች ናቸው። ረመዷን ደግሞ ከእስልምና ጾም ውስጥ ጉልሁ ክዋኔ እና የችግረኞችን የሕይወት ጊዜ መራብ እና መጠማት ለመጋራት ብሎም ራስን በመግዛት ከፈጣሪ እዝነት እና ረህመት ለማግኘት የሚከወን የሕዝበ ሙስሊሙ ታላቅ ክዋኔዎች ውስጥ አንዱ ነው።
የ1 ሺህ 445ኛ ዓመተ ሂጅራ የረመዷን ጾም ተጠናቆ ኢድን ለመቀበል ከአንድ ቀን ያልበለጠ ጊዜ ይቀረዋል። በወርኃ ረመዷን ከሚፈጸሙ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ውስጥ ዘካተል ፊጥር አንዱ ነው። ሼህ ኡመር አሊ የደሴ አረብ ገንዳ መስጅድ ምክትል ኢማም፣ የእስላማዊ ትምህርት መምህር፣ በደሴ ከተማ ኡለማ ምክር ቤት የፈተዋ ክፍል ኀላፊ ናቸው። በረመዷን፣ በዘካተል ፊጥር፣ በኢድ እና ተያያዥ እሥላማዊ አስተምህሮዎች እና ሥርዓቶች ላይ አጭር ማብራሪያ ሰጥተውናል።
ዘካተል ፊጥር ማለት ፈጥር ከሚለው የተወሰደ ሲኾን ዘካ (ምጽዋት) ማለት ነው። ረመዷን ሲጠናቀቅ የሚሰጥ እንደ ጨረቃዋ ሁኔታ 29 ወይም 30 ቀን ሲጾም ከቆየ በኋላ ረመዷን ሲጠናቀቅ (ሲፈጠር) ለዝቅተኛ ነዋሪዎች የሚሰጥ ምጽዋት መኾኑን ሼህ ኡመር አሊ ገልጸዋል። ዘካ በረመዷን በየቀኑ የሚፈጸም ቢኾንም ዘካተል ፊጥር በጾሙ ማጠናቀቂያ የሚከወን የበጎነት ሥራም ነው።
ይህ ሃይማኖታዊ ተግባር የተደነገገበት ምክንያት ለዝቅተኛ ነዋሪዎች ድጋፍ ለማድረግ እና ጾመኛው ራሱ በጾም ውስጥ የሚሠራቸው አንዳንድ እንከኖች ቢኖሩ ጾሙ ከእንከኖቹ እንዲጸዱለት እና በፈጣሪ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መኾኑን ሼህ ኡመር ገልጸዋል። ዘካተል ፊጥር በዓመተ ሂጅራ አቆጣጠር ሁለተኛው ዓመት ላይ የተጀመረ መኾኑን ሼህ ኡመር ጠቅሰው በመኾኑም እስካሁን ድረስ 1 ሺህ 443 ዓመተ ሂጅራ ዘካተል ፊጥር እንደተከወነ ገልጸዋል።
ዒድ አልፈጥር ከመድረሱ በፊት ሦስት ቀን ጀምሮ የሚፈጸመው ዘካተል ፊጥር የዒድ በዓሉ ቀን ወደ ዒድ ሶላት ከመወጣቱ በፊት እንደሚከወን ነው ሼህ ኡመር የተናገሩት። አንድ ሙስሊም ዘካተል ፊጥርን ለመከወን እንደ ዘካ የተገደበ የሃብት መጠን በላይ መኖር ሳይጠበቅበት ከአንድ ቀን ምግብ በላይ ትርፍ ካለው ዘካተል ፊጥርን ይሰጣል።
በኡለማ ደረጃ ዘካተል ፊጥር ምን እና እንዴት መሰጠት እንዳለበት በመመካከር ለመጅሊስ፤ መጅሊሱ በተዋረድ ለመስጊድ ኮሚቴ፤ በመቀባበል ለዘካተል ፊጥር የሚኾነውን ሰብስቦ ለሚገባቸው ዝቅተኛ ነዋሪዎች እንዲሠጥ ይደረጋል። በግለሰብ ደረጃም በአካባቢው ለሚያውቃቸው ዝቅተኛ ነዋሪዎች መስጠት እንደሚቻል ነው የተናገሩት።
እስልምና የዝቅተኛ ነዋሪዎችን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ስልቶችን ማስቀመጡን የገለጹት ሼህ ኡመር ”እስልምና አምላካዊ እና ሰማያዊ ሃይማኖት ከመኾኑ የተነሳ ፈጣሪ የፍጡራኑን ችግር ለመቅረፍ ከገንዘብ ጋር ተያይዞ የተደነገጉ ዘካዎች፣ ጾም ሲፈጠርም ለዝቅተኛ ነዋሪዎች እንዳይረሱ ረሃብ እንድንካፈል ነው ያዘዘን” ብለዋል። የረመዷንን ወር ስናስፈጥር ብንቆይም፣ በዒድ ዋዜማም ዘካተል ፊጥር ብንፈጽምም፣ በዒድ ቀንም ተመሳሳይ ችግረኞችን ይዞ መዋል እንዲሁም በሶደቃ ችግረኞችን መርዳት በእስልምና ሃይማኖት በጎ ምግባር ኾነው እንደሚተገበሩ አብራርተዋል።
ውኃ እሳትን እንደሚያጠፋው ሁሉ ለችግረኞች መርዳት እና መስጠት (ሶደቃ) ሀጢዓትን እንደሚያጠፋ ነብዩ አለይህ ወሰላም (ሰዐወ) በምሳሌ መናገራቸውን ገልጸዋል። ከፈጣሪ ዘንድ ሃጂር እንደሚያስገኝ ለሶደቃ የሚወጣውንም አላህ ይተካዋል ብለዋል። በተለይ ደግሞ ሰዶቃ ሚስጢራዊ ሲኾን የበለጠ ነው ብለዋል።
ስለኾነም እነዚህን ሃይማኖታዊ ድንጋጌዎች እና መርኾዎች በመተግበር ዘንድሮም እንደተለመደው ሁሉ የዝቅተኛ ነዋሪዎችን ችግር በመቅረፍ የአላህ ወስብአነ ወሰአላ(ሰዐወ) ትዕዛዛትን በመፈጸም የህሊና እርካታ ማግኘት እንደሚገባ አሳስበዋል። ሙስሊሙ ማኅበረሰብም አማኝነቱ የሚረጋገጠው የተራበ እና የተቸገረ ጎረቤቱን እና ወገኑን ሲያስብ እና ሲረዳ መኾኑን ነው ሼህ ኡመር የገለጹት። ”ስለዚህ ገንዘብ ያላችሁ እንረዳዳ፤ በአሁኑ ሰዓት ኑሮ ውድነት ከጣሪያ በላይ፤ ብዙ ዝቅተኛ ነዋሪዎች ከመደበኛ በታች የኾኑበት እና በጣም ዝቅተኛ ነዋሪ የሚባል ስም የምንሰማበት ጊዜ ላይ በመኾናችን በዚህ ላይ መረባረብ እና መተጋገዝ ያስፈልገናል” ሲሉ መተጋገዝ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!