
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ አፈ ጉባኤው በመልእክታቸው ረመዷን የእዝነት፣ የበረከት፣ የፍቅር እና የአንድነት ወር መኾኑን ገልጸዋል፡፡ በምእመኑ ዘንድ ፈጣሪ ሰላምን፣ በረከትን፣ እዝነትን እና ፍቅርን እንደሚያድል ይታመናል ነው ያሉት፡፡
ወሩ በመላው ሙስሊም ልብ ውስጥ ታላቅ ቦታ የሚሰጠው እና ከኢስላም አስተምህሮቶች ውስጥ አንዱ የኾነው ግዴታ የሚከወንበት መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በረመዷን ወር ሃይማኖታዊ ሕግጋቱ በሚያዘው መሠረትም የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፣ ተካፍሎ በመብላት፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በርህራሄ፣ በመተሳሰብ፣ በጽሞና እና በልባዊ እዝነት ያሳልፋሉ ነው ያሉት፡፡
ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ለሕዝቦች ዘላቂ ሰላም፣ አንድነት እና አብሮነት ጽኑ መሠረቶች ናቸው ያሉት አፈ ጉባኤው የዒድ አልፈጥር በዓል ሲከበር ለአንድነት እና ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት መኾን አለበት ብለዋል፡፡ አሁናዊ የሀገራችን ሁኔታ የሰላምን ዋጋ ባልተረዱ ኃይሎች ከዚህም ከዚያም በሚከሰቱ ግጭቶች ምክንያት ዜጎች ለከፋ ሕይዎት እና ለችግር እንዲዳረጉ ኾነዋል ነው ያሉት፡፡ ዜጎች ወደቀደመ ሰላማዊ ሕይዎታቸው እንዲመለሱ የሃይማኖቱ አስተምህሮ በሚያዘው መሠረት ሁሉም የእምነቱ ተከታዮች የተቸገሩትን በመደገፍ፣ በሕዝቦች መካከል ፍቅርን እና መተሳሰብን በማጽናት የበኩላችውን ድርሻ ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡
የተጀመረውን ሀገራዊ ልማት ዳር ለማድረስ እና የሀገርን ሰላም ለመጠበቅ መላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመደጋገፍ እና የአብሮነት እንዲኾንላችሁም መልካም ምኞታቸውን ማስተላለፋቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስፍሯል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!