
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ ዛሬ በፍኖተሰላም ከተማ ከጎጃም ኮማንድፖስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት እንደተናገሩት ጎጃምን ያምስ የነበረው ጽንፈኛ ኃይል ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል።
“ሰራዊቱ የሕዝቡን ሰላም ለማምጣት እና ሕግ ለማስከበር ባደረገው ስምሪት ጽንፈኛው ቡድን ቆሞ የመዋጋት ቁመናውን አጥቷል” ብለዋል።
ጽንፈኛው ቡድን በሕዝቡ ላይ ባደረሰው ግፍ ከሕዝብ ተነጥሏል ያሉት ጀኔራል አበባው በደረሰበት ሽንፈት ወደ ተራ ሽፍታነት ወርዷል፤ አደረጃጀትም የለውም ብለዋል። በዚህም ጽንፈኛ ቡድኑ ወደ ሽብር ሥራ ገብቷል ነው ያሉት። ጀኔራል አበባው እንዳሉት ሠራዊቱ በአሁኑ ሰዓት በተግባር የተፈተነ ግዳጅ የመፈጸም አቅሙም የዳበረ ኾኗል። ከፍተኛ ጽናት ያለው፣ የውጤት የበላይነት የያዘ፣ በአስተሳሰብም በተግባርም ተፈትኖ የጠነከረ ኃይል ሊኾን ችሏል።
የጎጃም ኮማንድፖስትም በተሰማራበት ቀጣና የተወጣው ተልዕኮ የጽንፈኛውን ኃይል በእጅጉ ያዳከመ፣ ዘራፊውን ቡድን ከሕዝብ የነጠለ እና የልማት እና ማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማት ሥራ እንዲጀምሩ ያስቻለ ውጤታማ ግዳጅ መወጣቱን አረጋግጠዋል።
ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው መከላከያ የጎጃም ኮማንድፖስት የፈጸመውን አኩሪ ተልዕኮ በትክክል ይመለከተዋል፤ ኮማንድፖስቱም ጀግንነቱን እና ያገኘውን ድል አስጠብቆ ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቅ ይገባዋል ብለዋል። መረጃው የጎጃም ኮማንድፖስት ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!