
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተለያዩ ወረዳዎች “እኛ ኢትዮጵያውያን ለሀገራችን ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልጽግና የበኩላችንን እንወጣለን” በሚል መሪ መልዕክት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል። በዚህ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ የጽንፈኛውን እኩይ ዓላማ የሚቃወም እና ለሀገር ሉዓላዊነት መስዋእትነት እየከፈለ የሚገኘውን የፀጥታ መዋቅር የሚያመሰግን ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ መደረጉ ተገልጿል።
ነዋሪዎች ሰንደቅ ዓላማቸውን ይዘው መፈክሮችን አንግበው በሰልፉ ላይ የተሳተፉ ሲሆን “በጥቂት ጽንፈኛ ኃይሎች አስተሳሰብ እና ድርጊት የሚበተን ሕዝብ እና ሀገር የለም፣ የላቀ ሕዝባዊ ተሳትፎ ለኢትዮጵያ ብልጽግና፣ ሀገራችን ወደ ከፍታ ለማሻገር ከለውጡ አመራር ጋር በጽናት እንቆማለን፣ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያችን እና የጥንካሬያችን መገለጫ ነው፣ መጋቢት 24 የኢትዮጵያ ትንሳኤ ማብሰሪያ ቀን ናት” የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮች በሰልፉ ላይ ተላልፈዋል።
በአጠቃላይ በዞኑ በላይ አርማጭሆ፣ በማዕከላዊ አርማጭሆ፣ በጭልጋ፣ በጠገዴ፣ በምዕራብ በለሳ፣ በኪንፋዝ በገላ ወረዳዎች እና በአይከል ከተማ አሥተዳደር ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ የተካሄደ ሲኾን ያለምንም የፀጥታ ችግር ተጠናቋል።
መረጃው፡- የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ነው፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!