ማስታወቂያ እና የሕግ ተጠያቂነት!

33

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ወቅቱ እየዘመነ በመምጣቱ ሰዎች የእጃቸውን ስልክ ተጠቅመው የተለያዩ መልዕክቶችን ሲያሰራጩ ይስተዋላል፡፡ ከሚዲያ ተቋማት ባለፈ ማስታወቂያዎች በማኀበራዊ ትስስር ገጾች ሲሰራጩ ይስተዋላል፡፡ ማኅበራዊ ትስስር ገጽን ለበጎ ዓላማ በተለይም ለማስታወቂያ ማስተላለፊያነት በመጠቀም የሚገኘው በጎ ነገር እንዳለ ኾኖ ጉዳቱም አሁን ላይ ከፍተኛ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡

በተለይም ገቢ ለማግኘት በሚል ሰዎች በብዛት በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ማስታወቂያ ሲያስተዋውቁ መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡ የማኅበራዊ የትስስር ገጾችን በመጠቀም ትክክለኛ ያልኾነን ነገር የሚሠሩ ማስተወቂያዎች እየተበራከቱ ናቸው፡፡ በእነዚህ ማስታወቂያዎችም ተታሎ ብዙ ሰው ሲጎዳ ይስተዋላል፡፡
በብዙሃኑ ዘንድ የማይዘነጋ አንድ ክስተት ብናነሳ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎችን ለመመልከት ወደ ደቡብ አፍሪካ ትሄዳላችሁ በሚል የተሠራው የተሳሳተ ማስታወቂያ ብዙዎችን ስለማጭበርበሩ ይገለጻል፡፡

ይህም ጉዳይ ወደ ፍትሕ ተቋማት አምርቶ እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡ የተሳሳተ ማስታወቂያ መንገርም ኾነ ማስነገር በሕግ የሚያስጠይቅ ነው ይላሉ ለአሚኮ የሕግ ማብራሪያ የሰጡት ዳኛ ነጸረ ወርቁ፡፡ ዳኛ ነጸረ እንደሚሉት በአዋጅ ቁጥር 759/2004 አንቀጽ 27 “ሀ” መሠረት ማንኛውም ማስታወቂያ አሰራጭ ወይም ወኪል ማስታወቂያውን እንዲነገርለት የተፈለገው ነገር ትክክለኛነት እና ከሚመለከተው አካል ሕጋዊ ፈቃድ ስለማግኘቱ ማረጋገጥ ይኖርበታል ይላሉ፡፡

ማስታወቂያው በቀረበበት አግባብ ሕግን የማይተላለፍ መኾኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ማስታወቂያው ተነግሮ ያመጣው ጉዳት ቢኖር እና ክስ ቢቀርብበት ማስታወቂያውን በአሰራጨው አካል ላይ በአዋጅ ቁጥር 759/2004 አንቀጽ 34/1 “ሀ” ላይ ከ10 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር ከሚጣለው ቅጣት በተጨማሪም ማስታወቂያው በመሠራቱ የተገኘው ሃብት እንዲወረስ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡ በተጨማሪም ጉዳዩ በወንጀል የሚያስቀጣ ከኾነም እንደወንጀሉ ሁኔታ ሊታይ የሚችል እንደኾነ ነው የነገሩን

በምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጦም የሚያድር መሬትም፤ ሰውም የለም
Next articleሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ተካሄደ፡፡