
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሁለተኛው ዙር መስኖ አፈጻጸም 50 በመቶ ደርሷል፡፡ በ2016 ዓ.ም 110 ሺህ 690 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዷል፡፡ አስካሁንም 55 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል፡፡ በሥራው ላይ 159 ሺህ አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል፡፡
አርሶ አደር ሻረው በላይ ይባላሉ፡፡ በሰሜን ጎጃም ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ የኩድሚ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ የቆጋ የመስኖ ግድብ ከሚሸፍነው 7 ሺህ ሄክታር ማሳ ውስጥ ሦስት ገመድ መሬት አላቸው፡፡
አርሶ አደር ሻረው የቆጋ ግድብ ሥራ ሲጀምር ጀምሮ ወደ መስኖ ልማት ሥራ ገብተዋል፡፡ በማሳቸው ላይም እያቀያየሩ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ ጥቅል ጎመን እና ድንች ከዓመት ሦስት ጊዜ ያመርታሉ፡፡ በሚያገኙት ምርትም ቤተሰቦቻቸውን በአግባቡ ያስተዳድራሉ፣ ልጆቻቸውን አስተምረው ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡
ሠርተው ባገኙት ገንዘብ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ ገዝተዋል፣ ዘመናዊ መኖሪያ ቤትም ገንብተዋል፡፡በ2016 ዓ.ም መሬታቸውን በስንዴ እና በድንች ሰብል ሸፍነዋል፡፡ ድንቹን አንስተው ሽንኩርት ተክለዋል፡፡ በቀጣይም ስንዴውን በማንሳት ከመኸር ቀድሞ የሚደርስ ሰብል ለመዝራት ተዘጋጅተዋል፡፡
በአርሶ አደር ሻረው ሰፈር ጦም የሚያድር መሬትም፣ ሰውም የለም፡፡ መሬት ጦም አያድርም፤ አንዱ ሰብል ሲነሳ ሌላው ይተካል፡፡
የቆጋ ግድብ ላይ የተቋቋመው ኅብረት ሥራ ማኅበር ውኃው በሥርዓት እንዲመራ እና በአግባቡ ጥቅም እንዲሠጥ እያደረገላቸው ነው፡፡ አሁን በአንድ ሰው ተራ ሌላ ሰው ማጠጣት የለም ይላሉ፡፡አርሶ አደር ሻረው የምርጥ ዘር እና የግብዓት አቅርቦት እጥረት እየገጠማቸው እንደኾነ ገልጸው በተለይ “ሊሙ” የበቆሎ ዘር በማጣታቸው አካባቢያዊ ዘር መጠቀማቸውን ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልት እና ፍራፍሬ ባለሙያው አወቀ ዘላለም በ2016 ሁለተኛው ዙር የበጋ መስኖ የሥራ አንቀሳቃሴ በወቅቱ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ አስካሁንም የዕቅዱን 50 በመቶ በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል፡፡ በ2016 ዓ.ም 110 ሺህ 690 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 55 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል ነው ያሉት፡፡ በሥራው ላይ 159 ሺህ አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል ነው ያሉት፡፡
ከ176 ሺህ 390 ኩንታል በላይ ማዳበሪያ እና 21 ሺህ 590 ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ መዋሉንም አቶ አወቀ ገልጸዋል፡፡አርሶ አደሮች ማሳቸውን በማለስለስ ወደ ሁለተኛ ዙር መስኖ መግባታቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ቀሪው ማሳ በቀጣዮቹ ሳምንታት እንደሚዘራም አንስተዋል፡፡
አርሶ አደሮች በማጥለቅለቅ ከማጠጣት ወጥተው በመሥመር እንዲያጠጡ እና አሲዳማነትን መከላከል እንዳለባቸውም አስታውሰዋል፡፡
ቀጣይ ሁለተኛው ዙር መስኖን ማሳን በማለስለስ መዝራት፣ የውኃ እጥረት ችግር እንዳይገጥም ውኃን በአግባቡ መጠቀም ተገቢ መኾኑንም መክረዋል፡፡አርሶ አደሮች ውኃን ከማጥለቅለቅ ማጠጣት ወጥተው በመሥመር እንዲያጠጡ እና አሲዳማነትን መከላከል እንዳለባቸውም አስታውሰዋል፡፡
ከሁለተኛው ዙር መስኖ ባሻገር በአንደኛው ዙር መስኖ 285 ሺህ 388 ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑንም ተናግረዋል፡፡ እስካሁንም 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሠብሠቡንም አቶ አወቀ አብራርተዋል፡፡ አርሶ አደሮች የሚፈልጉትን ነዳጅ በሚፈልጉት ወቅት ስለማያገኙ በምርታማነት ላይ ችግር እየተፈጠረ መኾኑን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡
አትክልት እና ፍራፍሬ ወቅታዊ ሰብል በመኾኑ ጉዳት ሊደርስበት ስለሚችል የሚመለከተው አካል ስርጭቱን ፍትሐዊ በማድረግ ሊከሰት የሚችለውን የምርት መቀነስ መከላከል እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ግድብ በሌለባቸው አካባቢዎች ያሉ አርሶ አደሮች በነዳጅ እጥረት እየተፈተኑ መኾናቸውን የገለጹት ባለሙያው ችግሩ እንዲቀረፍላቸው ሁሉም የሚመለከተው አካል ለችግሩ መፍትሔ እንዲያመጣ ጠይቀዋል፡፡አርሶ አደሮች ተባይን እና በሽታን እንዲከላከሉም አቶ አወቀ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!