
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ 1 ሺህ 445ኛውን ዓመተ ሂጅራ የዒድ አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ለችግረኛ ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ አድርጓል። በድጋፉ ለ20 ወገኖች ለእያንዳንዳቸው ሦስት ሊትር ዘይት፣ 12 ኪሎ ግራም ማካሮኒ እና አንድ ዶሮ ተሰጥቷል።
ወይዘሮ አገር አማን እና አቶ አሊ አህመድ በተደረገላቸው ድጋፍ ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል። ለበዓል መዋያ ይቸገሩ እንደነበር እና በድጋፉ አማካይነትም በዓልን ደስ ብሏቸው ስለሚያከብሩም አመስግነዋል። ሌሎች ዝቅተኛ ኑሮ የሚመሩ አካላት ድጋፍ ቢያገኙ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘዉዱ የበዓል መዋያ ስጦታው አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሙስሊም ወገኖች የዒድ አልፈጥር በዓልን እንዲያከብሩ ማድረግ እና ለሌላውም ዓርእያ ለመኾን ነው ብለዋል።
ወገናዊነትን ለማጠናከር እና “እንኳን አደረሳችሁ” ለማለት መኾኑንም ገልጸዋል ወይዘሮ ሰብለ። የኑሮ ውድነት ስላለ ችግረኛ የኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ሌላውም ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ ነው ወይዘሮ ሰብለ ያሳሰቡት።
ድጋፉ ከባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር፣ ከማኅበረሰቡ እና ከሠራተኞች የተገኘ መኾኑን እና በዓልን በጋራ የማክበር እና ተባብሮ የመኖር እሴታችንን ለማጠናከር ነው ሲሉም ኀላፊዋ ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!