
ባሕር ዳር: ሚያዚያ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጎጃም ኮማንድፖስት ወቅታዊ የሰላም፣ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎች አፈፃፀም እና በቀጣይ በሚከናወኑ ወቅታዊ ተግባራት ዙሪያ በፍኖተሰላም ከተማ እየገመገመ ነው። በመድረኩ የተገኙት በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይርጋ ሲሳይ ከሰሞኑ በፍኖተሰላም ከተማ በመማር ላይ ባሉ ተማሪዎች ላይ እና በገበያ ላይ ቦንብ በመወርወር በንጹሃን ላይ ጉዳት ያደረሰውን የጽንፈኛውን ድርጊት አውግዘዋል።
ጽንፈኛው ኀይል እየፈፀመ ያለው ድርጊት የሕዝባችንን ባሕል እና እሴት የማይመጥን መኾኑን ገልጸው በፀጥታ ኀይሉ እና በአመራሩ ጥረት የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች በመኾኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል። በግምገማ መድረኩ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት በመኾኑ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና ቀጣናው ወደ ተሟላ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እንዲመለስ እየተሠራ መኾኑ ተመልክቷል።
በመድረኩ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር)፣ ሌተናል ጀኔራል መሀመድ ተሰማ የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ እና የጎጃም ኮማንድፖስት ሰብሳቢ፣ የምዕራብ ጎጃም፣ የሰሜን ጎጃም፣ የምስራቅ ጎጃም፣ የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና የደብረ ማርቆስ ከተማ የኮማንድፖስት አባላት ተገኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!