ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲያከብር የጋራ ግብረ ኃይሉ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገለጸ፡፡

19

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲያከብር የፀጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ከወዲሁ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ተግባር መግባቱን ገልጿል፡፡ ግብረ ኃይሉ የኢድ አል ፈጥር በዓልን አስመልክቶ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፏል፡፡

የጋራ ግብረ ኃይሉ ሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲያከብር በሁሉም ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አሥተዳደሮች ከወዲሁ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ተግባር በመግባት ተልዕኮውን በተገቢው እየተወጣ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ግብረ ኃይሉ ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብም ለሰላም እና ደኅንነት እንቅፋት የኾኑ ነገሮችን ለማስወገድ በሚካሄደው የፀጥታ ማስከበር ሥራ ውስጥ በባለቤትነት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስቧል፡፡

ሕዝቡ የአካባቢውን ሰላም እና ደኅንነት የሚያደፈርሱ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት እና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ከግብረ ኃይሉ ጎን ኾኖ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ግብረ ኃይሉ ጥሪ አቅርቧል፡፡ የሀገርን እና የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ በማበርከት የኢትዮጵያን ልዕልና ለማረጋገጥ ሌት ተቀን እየሠሩ ላሉ በግዳጅ ላይ ለሚገኙ የፀጥታ አካላት አመራሮች እና አባላትም ግብረ ኃይሉ ምሥጋና አቅርቧል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የኢድ አልፈጥር በዓል መዋያ ድጋፍ አደረገ።
Next article“በጽንፈኛው ኀይል እየፈፀመ ያለው ድርጊት የሕዝባችንን ባሕልና እሴት የማይመጥን” አቶ ይርጋ ሲሳይ