የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የኢድ አልፈጥር በዓል መዋያ ድጋፍ አደረገ።

26

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 1/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ 1 ሺህ 445ኛው ዓመተ ሂጅራ የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ለችግረኛ ሙስሊም ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ አድርጓል። ለ40 ችግረኞች ለእያንዳንዳቸው 10 ኪሎ ግራም ፊኖ ዱቄት፣ 10 ሊትር ዘይት፣ አንድ ዶሮ እና አንድ ብርድ ልብስም ተሰጥቷቸዋል።

የቢሮው ኀላፊ ብርቱካን ሲሳይ ቢሯቸው ድጋፉን ያደረገው የኢድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ችግረኛ ሙስሊም ወገኖች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ በማሰብ መኾኑን ገልጸዋል። ችግረኛ ወገኖችን የመደገፉ ሥራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅሰው ድጋፍ ያደረጉ አካላትንም አመሥግነዋል።
በባሕር ዳር ከተማ የሰላም በር መስጊድ ኢማም ሼህ መሐመድ አብራር በዓሉን አስመልክቶ ችግረኛ ወገኖችን ማስደሰቱ በጣም ጥሩ መኾኑን ጠቅሰው ”አሏህ የሚወደው” ይህንኑ ነው ብለዋል።

”ሃይማኖታችን የሚለው ትንሽም ነገር ብትኾን ስጡ” ነው ያሉት ሼህ መሐመድ ችግረኞችን መደገፉ መለመድ አለበት ብለዋል። ምስኪኖች ልባቸው የሚነካው በዓል ሲመጣ ነውና ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ችግረኞች ተደስተው እንዲውሉ በማድረጉ ምሥጋና ይገባዋል ብለዋል። ሌሎቹ ቢሮዎችም ይህንን አርዓያነት እንዲከተሉ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪ ፋሲል ታየ በዚህ ጊዜ አንዱ ለአንዱ መተሳሰብ አስፈላጊ መኾኑን ጠቅሰው ቢሮው ያደረገው ድጋፍ የሚበረታታ መኾኑን ገልጸዋል። የድጋፉ ተጠቃሚ ወይዘሮ ከድጃ ሰይድ ይህንን ድጋፉ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል። ለቀሩት ሕጻናት አካል ጉዳተኞች እና አቅመ ደካሞችም ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጽንፈኝነት የወለደው ፈተናዎች ቢገጥሙንም፣ ፈተናዎችን ወደ እድል፣ አቅማችንን ወደ ውጤት በመቀየር የብልጽግና ጉዟችንን እናስቀጥላለን” አቶ ይርጋ ሲሳይ
Next articleሕዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲያከብር የጋራ ግብረ ኃይሉ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ገለጸ፡፡