“ጽንፈኝነት የወለደው ፈተናዎች ቢገጥሙንም፣ ፈተናዎችን ወደ እድል፣ አቅማችንን ወደ ውጤት በመቀየር የብልጽግና ጉዟችንን እናስቀጥላለን” አቶ ይርጋ ሲሳይ

37

በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተካሄዱ የድጋፍ ሰልፎችን በማስመልከት መልእክት አስተላልፈዋል። እንደክልል ጽንፈኝነት የወለደው ፈተናዎች ቢገጥሙንም፣ ፈተናዎችን ወደ እድል፣ አቅማችንን ወደ ውጤት፣ ተግዳሮቶች ወደ ስኬት በመቀየር፣ በመተሳሰብና በወንድማማችነት እጅ ለእጅ በመያያዝ ሕዝባችንን ከጎናችን በማሰለፍ የብልጽግና ጉዟችንን እናስቀጥላለን።

ሀገራዊ ለውጡን የወለደው የብልጽግና ፓርቲ የሀገራችንን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስብራት በዘላቂነት መፍታት የሚቻለው ሀገራዊ አንድነታችንን በሚያጠናክርና በወንድማማችነት፣ በእህትማማችነት ማዕቀፍ ውስጥ በማየት ሁሉን አቀፍና ዴሞክራሲያዊ መፍትሔ ማምጣት እንደሚቻል በፅኑ ያምናል። ስለዚህ ሀገራዊ አንድነታችን በሕግ፣ በአሠራርና በተቋም ደረጃ ዋና አጀንዳ በማድረግ እየሠራን እንገኛለን።

ይሁን እንጅ በክልላችን ጽንፈኝነት የወለደውን አስተሳሰብ የሚጋሩ አካላት የክልላችን ሕዝብ ከመላ ኢትዮጵያውያን ጋር ታግሎ ያመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍ ብሎም ክልሉን ለማፍረስ ከታሪካዊ ጠላቶቻንና ሰላምን ከማይፈልጉ የውስጥና የውጭ አካላት ጋር በመናበብ እኩይ ተግባር ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል፡፡

ስለሆነም ብልፅግና ፓርቲ መላ የክልላችን ሕዝብ በማሳተፍ በክልላችን ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና የጽንፈኞችን እኩይ ተግባር ለማክሸፍ በየደረጃው የሚገኝ አመራርና ሕዝቡ እንዲሁም ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን በከፈለው መስዋዕትነት ክልሉን ከሴረኞችና ጽንፈኛ ኀይሎች ከንቱ ህልም ማክሸፍ ተችሏል፡፡

በመሆኑም በፓርቲያችን ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ብልፅግና የማይቀር መሆኑን ያረጋገጡ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ድሎችን አስመዝግበናል። በክልላችንም ውስጥ ትልቅ የብልጽግና አሻራ መተከሉን ዛሬ በርካታ የክልላችን ከተሞች ድጋፍ ሰልፍ ሕዝቡ አደባባይ ወጥቶ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

በቀጣይም ምንም እንኳ በጉዟችን መሀል እንደክልል ሰው ሰራሽ እና ጽንፈኝነት የወለደው ፈተናዎች ቢገጥሙንም፣ ፈተናዎችን ወደ እድል ቀይረን፣ አቅማችንን ወደ ውጤት፣ ተግዳሮቶች ወደ ስኬት በመቀየር፣ በመተሳሰብና በወንድማማችነት እጅ ለእጅ በመያያዝ ጉዟችንን ሕዝባችንን ከጎናችን በማሰለፍ እንቀጥላለን።

በየደረጃው የሚገኙ የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎችም አንድነታችንን በማጠናከር ፅንፈኝነትን፣ ውጤታማ አለመሆንን፣ ሌብነትን እና ሙስናን በመታገል ፈታኝ የሆነውን ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ በክልላዊ ኮንፈረናሳችን የገባነውን ቃል እውን እናደርጋለን።

በዚህ ሂደት የክልላችን ነዋሪዎች ከጎናችን መሆናችውን በሕዝባዊ ማዕበል በታጀበ ሰልፍ አረጋግጣችሁልናልና ለሰጣችሁን እውቅና የላቀ ክብርና ምስጋና አለን። በቀጣይም በክልላችን ዘላቂ ሰላምን በማጽናት ሁለንተናዊ ለውጥን ለማረጋጥ ሕዝቡ ጋር ተቀራርበን ለመስራት የምንቀሳቀስ ሲሆን ለዴሞክራሲ መጠናከር የማይተካ ሚና ያላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሁሉም የዴሞክራሲ ተቋማት ለክልላችን ለኢትዮጵያችንና ለሕዝቦቿ ብልፅግና በጋራ እንድንሠራ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

Previous article“ሕዝብ ተናግሯል፤ መንግሥትም ያዳምጣል” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Next articleየአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ወገኖች የኢድ አልፈጥር በዓል መዋያ ድጋፍ አደረገ።