“ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ለተከናወኑ የልማት ሥራዎች አድናቆት እና እውቅና፤ ለቀሪ ሥራዎች ደግሞ የቤት ሥራ የሰጠ ነው” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)

60

ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በ96 ከተሞች የተካሄደው ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ገልጿል። የድጋፍ ሰልፉን በማስመልከት መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ መንግሥት ባለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት ያከናወናቸውን የልማት ሥራዎች እውቅና የሚሰጥ ነበር ብለዋል። ሰልፉ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረስ አስመልክቶ የሕዝብ ደስታ የተገለጸበት ጭምር ስለመኾኑም ገልጸዋል። በሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ ክልሉን ወደ ምስቅልቅል ለማስገባት የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞች የተወገዙበት እና መንግሥት እያከናወነው ያለው ጠንካራ ሕግ የማስከበር ሥራም የተደነቀበት ነበር ነው ያሉት።

ዶክተር መንገሻ “ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ለተሠሩት የልማት ሥራዎች አድናቆትና እውቅና፣ ለቀሪ ሥራዎች ደግሞ የቤት ሥራ የሰጠ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ በተራማጅ አመራሮች የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን እውቅና ከመስጠቱ በተጨማሪ በቀጣይም ሕዝብን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ሥራዎች እንዲከናወኑ ለመንግሥት አመራሩ የቤት ሥራ የሰጠ ነው ብለዋል። በሰልፉ ሕዝቡ በለውጡ የተመለከታቸውን እና ተጠቃሚ የኾነባቸውን የልማት ሥራዎች ተገንዝቦ ያመሰገነበት እንደኾነም በመግለጫቸው አመላክተዋል።

በተለይም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከነበረበት ውስብስብ አፈጻጸም ተላቅቆ በአዲስ አስተሳሰብ እና አሠራር በማለፍ ወደመጨረሻው ምዕራፍ መድረሱ ሕዝብን ያስደሰተ እና በድጋፍ ሰልፉ ላይም ሰፊ አድናቆት እና መልዕክት የተስተጋባበት ነበር ብለዋል።

ዶክተር መንገሻ የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ጽንፈኝነትን እና አክራሪ ብሔርተኝነትን በመታገል ረገድ ትልቅ ትምህርት የሰጠ ስለመኾኑም ገልጸዋል። ዋልታ ረገጥ የኾኑ የጽንፈኝነት አስተሳሰቦችን በማረም ኅብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን በመገንባቱ ረገድ ሕዝቡ ያለውን ጽኑ ፍላጎት የገለጸበት ሰልፍ እንደኾነም ጠቁመዋል።

በጽንፈኝነት አካሄድ ክልሉ እና ሕዝቡ ዋጋ እየከፈለ ነው፤ ነገን በተስፋ በሚያልሙ ንጹሃን ተማሪዎች ላይ ጭምር ሽብር በመፍጠር ከሰው የማይጠበቅ ድርጊት የሚፈጽሙ ጽንፈኞች ተስተውለዋል፤ በድጋፍ ሰልፉ የወጣው ሕዝብ ይህንን በጽኑ አውግዟል ነው ያሉት በመግለጫቸው።

የድጋፍ ሰልፉ በርካታ ትምህርቶችን ሰጥቶ ያለፈ እንደኾነም ዶክተር መንገሻ ገልጸዋል። በአማራ ክልል ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት የሚደረገው ሕግ የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ተሠርተው እንዲጠናቀቁ እና ሕዝብ ተጠቃሚ እንዲኾን በትጋት መሠራት እንዳለበት ግንዛቤ የተጨበጠበት ሰልፍ እንደነበርም ገልጸዋል።

ዶክተር መንገሻ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የአማራ ክልል ሕዝብ ለሰላም እና ለልማት ያለውን ቀናኢነት በመገንዘብ ክልሉ ዘላቂ ሰላምና ኅብረ ብሔራዊነት ለመገንባት የሚያደርገውን ትግል እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሁመራ ከተማ የለውጡን ስድስተኛ ዓመት በማስመልከት ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተካሔደ።
Next articleMaxxansa Gaazexaa Hirkoo: Bitootessa 30/2016