
ሁመራ፡ መጋቢት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሁመራ ከተማ ነዋሪዎች ሀገራዊ ለውጥን ተከትሎ ነጻነታቸውን ማግኘት እንደቻሉ እና የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን በመጠቀም ባሕልና እሴታቸውን እያስቀጠሉ እንደሚገኙ አንስተዋል።
በዛሬው ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ከተላለፉ መልእክቶች መካከል፦
👉ለሀገራችን ሰላም እና አንድነት የማንከፍለው ዋጋ አይኖርም!
👉ሰላም በእያንዳንዳችን ቤት ናት!
👉የላቀ ሕዝባዊ ተሳትፎ ለኢትዮጵያ ብልጽግና!
👉አማራ ነን እንጅ አማራ እንሁን አላልንም!
👉 የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ አንድ እንጅ ሁለት ሦስት ጥያቄ የለውም እኛ አማራ ነን!
👉ታሪካችን ፣ተፈጥሯዊ ማንነታችን፣ ሥነ ልቦናችን አማራ ነን ” በማለት ድምጻቸውን አሰምተዋል።
የለውጡ መንግሥት የአካባቢውን ሕዝብ የዘመናት ጥያቄ በመመለስ በሕግ ነጻነታቸውን እንዲያጸናላቸውም በሰልፉ ላይ ጠይቀዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ በሀገራዊ ለውጡ ነጻነቱን ማግኘት እንደቻለ አንስተዋል።
በለውጡ ሂደትም ለዘመናት የተነፈገውን ባሕሉን እና ወጉን ማስቀጠል እንደቻለ አንስተው ሕዝብ የአፍ መፍቻ ቋንቋውን ተጠቅሞ በነጻነት እየኖረ ነው ብለዋል። በቀጣይም የሕዝቡን የማንነት ጥያቄ በሕግ አግባብ አውቅና እንዲያገኝ የዞኑ አሥተዳደር በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ኅብረተሰቡ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብን አስመልክቶ የሚሰራጩ የሀሰት መረጃዋችን ባለመቀበል የአካባቢውን ሰላም እንዲያስጠብቅም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያውያን የአንድነት ምልክት የኾነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አያሌ ፈተናዎችን አልፎ በለውጡ ኃይል አመርቂ ሥራ ለመገባደድ በመቃረቡ ሕዝቡ ያለውን ድጋፍ መግለጹን ነው የተናገሩት፡፡ ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ብሎም የአካባቢውን ሰላም አስጠብቆ መዝለቅ ዓላማ ያደረገ ሰልፍ ስለመካሄዱም አብራርተዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!