
ሰቆጣ፡ መጋቢት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ሰቆጣ ከተማ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል። በድጋፍ ሰልፉም የሰቆጣ ከተማ እና የሰቆጣ ዙርያ ወረዳ ነዋሪዎች፣ የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች ተሳትፈዋል። በሰልፉ የተሳተፉት አቶ ጌጡ አለምነው በዋግ ኽምራ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲጠናቀቁ ሰላም ጠል የኾኑ ኃይሎችን ከመንግሥት ጎን ኾነን መመከት ይገባናል ብለዋል።
አቶ ጌጡ ባለፉት ዓመታት ያየናቸውን የአስፖልት እና ሌሎች የልማት እንቅስቃሴዎችን በጦርነቱ ምክንያት እስከአሁን ሳይጠናቀቁ መቆየታቸውን ተናግረዋል። የዋግ ሕዝብ ሰላም ወዳድ ነው፤ ከመንግሥት ጎን በመቆም ሰላሙን ለመጠበቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ለድጋፍ መውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
“ሰላም ጠል የኾኑ ኃይሎች ዓላማቸው ሕዝብን ማሰቃየት ነው” ያሉት ደግሞ የሰቆጣ ከተማ ነዋሪው አቶ መልካሙ አበራ ናቸው። ጽንፈኛውን ቡድን በመቃወም በመንግሥት የተጀመሩ ልማቶች እንዲቀጥሉ እንፈልጋለን ሲሉ ገልጸዋል። በድጋፍ ሰልፉ ላይ ንግግር ያደረጉት የሰቆጣ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መላሽ ወርቃለም ሰላም እና ልማት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ሰላም ከሌለ ደግሞ ልማት አይኖርም ብለዋል።
“በከተማችን ብሎም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የተጀመሩ የትምህርት፣ የመንገድ እና የተቋማት ግንባታዎችን በተያዘላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ ሰላም ጠል ኃይሎች እያደናቀፉ ይገኛሉ” ነው ያሉት፤ የዋግ ሕዝብ ከመንግሥት ጎን በመኾን ያመጣውን ሰላም ተከትሎ መንግሥት በአፋጣኝ የጀመራቸውን የልማት እንቅስቃሴዎች እንዲያስቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ሹመት ጥላሁን በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጋራ የወለደው የለውጡ መንግሥት በዓይን የሚታዩ ልማቶችን እየሠራ ይገኛል ብለዋል። ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ከውስብስብ የግንባታ ሥራ በማላቀቅ ወደ ፍጻሜ ምዕራፍ መድረሱን አቶ ሹመት ገልጸዋል፡፡ “በበሰለ ዲፕሎማሲያዊ ብቃት የሀገርን ገጽታ የቀየረውን መንግሥታችንን መደገፍ ልማትን ማፋጠን ነው” ብለዋል። በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳዳር ያለውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም በመንግሥት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን እንዲጠናቀቁ በሕዝባችን ስም እንጠይቃለን ብለዋል። በሰቆጣ ከተማ የተካሄደው የድጋፍ ሰልፉም በሰላም ተጠናቋል።
በደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!