
ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን የለጋምቦ ወረዳ እና የአቀስታ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች ሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በአቀስታ ከተማ አካሂደዋል፡፡
በሰልፉ ላይ ለክልላችን ሰላም በሕብረት እንቆማለን፣ በጥቂት ጽንፈኛ ኃይሎች አስተሳሰብ እና እኩይ ድርጊት የሚበተን ሀገር እና ሕዝብ የለንም፣ ክልላችንን በውክልና ጦርነት ማፍረስ አይቻልም፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራችን ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልጽግና የበኩላችንን እንወጣለን የሚሉ እና ሌሎች መልዕክቶች ተላልፈዋል።
በተጨማሪም “ሀገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያን የታደገ እና ሕልውናችንን ያስቀጠለ ነው፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአንድነታችን እና የጥንካሬችን መገለጫ ነው፣ ውስጣዊ ሰላማችንን በማጽናት ውጫዊ ተጽዕኖዎችን በድል እንወጣለን፣ የክልላችንን አንጻራዊ ሰላም በአጭር ጊዜ ወደ ዘላቂ ሰላም እናሸጋግረዋለን የሚሉ ድምጾችም ተሰምተዋል፡፡
የሰልፉ ተሳታፊዎች ጉድለቶችን በማረም በለውጡ የተገኙ ድሎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ከለውጡ መሪዎች ጋር በጽናት መቆም እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ሰልፉ ላይ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ መሪዎች፣ የወረዳው እና የከተማው ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ባለሃብቶች እና የንግዱ ማኅበረሰብን ጨምሮ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈውበታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!