ሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ በወረታ ከተማ ተካሂዷል፡፡

17

ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የወረታ ከተማ እና የአካባቢዋ ነዋሪዎች ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ አካባቢያቸውን ሰላም ለማድረግ ከለውጥ አመራሩ ጋር እየሠሩ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ሰልፈኞቹ ባለፉት ዓመታት ለውጥ መታየቱን ገልጸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከሰተው የሰላም እጦት ልማታቸው አደጋ ውስጥ ወድቆ መቆየቱን ነው ያስረዱት፡፡

የወረታ እና የአካባቢው ሕዝብ ፍላጎቱ ሰላም እንጅ ጦርነት አለመኾኑንም ነው ያብራሩት፡፡ አካባቢውን ሰላም ለማድረግም መሥራታቸውን አስረድተዋል፡፡ በተከሰተው የፀጥታ ችግር የሰው ሕይዎት መጥፋቱን እና ንብረትም መውደሙን አስገንዝበዋል፡፡ በቀጣይ ችግሮች ሲኖሩ በውይይት መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ ከእስካሁኑ ጥፋት ትምህርት መወሰዱንም ነው ያስረዱት፡፡

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት የወረታ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እሸቱ ሞላ ወረታ የልማት እና የሰላም ተምሳሌት የኾነች ከተማ ስለመኾኗ ተናግረዋል፡፡ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እሸቱ ባለፉት ወራት ለከተማዋ የማይመጥን የፀጥታ ችግር ገጥሞ እንደነበረ ገልጸዋል፡፡ በፀጥታ ችግሩም የሰው ሕይዎት መጥፋቱን ንብረትም መውደሙን ነው የተናገሩት፡፡

የለውጡ መንግሥት በከተማዋ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ለውጥ የሚያመጡ የልማት ሥራዎችን ስላማከናወኑ አብራርተዋል፡፡ በተለይም በከተማዋ ውስጥ የኃይል አቅርቦት፣ የውኃ አቅርቦት፣ የደረቅ ወደብ ግንባታ ሥራ፣ የአትክልት ልማት ሥራ ማሳለጫ ሼድ ግንባታን ጨምሮ ልዩ ልዩ የልማት ተግባራትን ማከናወኑን እና በዚህም ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ወደፊትም ሕዝቡ ሰላሙን ከለውጡ አመራር ጋር በመቀናጀት ከጠበቀ ከተማዋን የሚመጥን የመንታ መንገድ ግንባታ፣ የወረታ ግብርና ኮሌጅ ወደ ዩኒቨርሲቲ አድጎ የአካባቢውን ኅብረተሰብ ተጠቃሚ የማድረግ፣ የአዲስ የውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ እንዲገነባ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ እሸቱ የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በውይይት እና በንግግር የሚፈቱ በመኾናቸው በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ውስጥ ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱ እንደሚሠሩም ነው ያስገነዘቡት፡፡ ከንቲባው ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ በወልድያ ከተማ ተካሄደ፡፡
Next articleሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በደቡብ ጎንደር ዞን በላይ ጋይንት ወረዳ እና ነፋስ መውጫ ከተማ ተካሂዷል፡፡