ሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ በወልድያ ከተማ ተካሄደ፡፡

23

ወልድያ: መጋቢት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰልፉ ላይ የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው ተሳትፈዋል፡፡ በሰልፉ ከተጠቀሱት መፈክሮች መካከል ለሀገራችን ሰላም እና አንድነት በጋራ እንቆማለን፤ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድል እና ስኬት የአባቶቻችንን ገድል የደገምንበት ታሪካዊ አደራችን ነው፤ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም የሚሉ ናቸው፡፡

ለሰልፉ ታዳሚዎች ንግግር ያደረጉት የወልድያ ከተማ ተቀዳሚ ምትል ከንቲባ ዱባለ አብራሬ ከለውጡ በኋላ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በስኬት ግንባታው እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ወልድያ ከተማን የለውጡ ተቋዳሽ ለማድረግ ልምላሜዋን ጠብቀን፣ መሰረተ ልማቷን ገንብተን፣ ኢንቨስትመንቷን አስፋፍተን ለነዋሪዎቿም ኾነ አልፈው ለሚሄዱ እንግዶቿ ምቹ ለማድረግ እየሠራን ነው ብለዋል።

በሌሎች አካላት የጠላነው የጭካኔ ፖለቲካ የራስን ሃሳብ በሌሎች ላይ በኃይል ለመጫን በሽምቅ በሚገድል ቡድን ምክንያት የንጹሐን ሕይዎት ጠፍቷል፤ የኑሮ ውድነት ተባብሷል፤ ሥራ አጥነትም ጨምሯል፤ በርካታ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
ነገር ግን ይህን ችግር ምክንያት አድርገን ሳንቀመጥ የልማት ሥራዎችን እየሠራን ነው ያሉት።

በመሰረተ ልማት ዘርፍ በድምሩ 18 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ እየሠራን ነው ሲሉ በንግግራቸው ገልጸዋል ከንቲባው። የመብራት እና የውኃ አቅርቦት ለማሻሻል ሠርተናል። የትምህርት፣ የጤና፣ የድልድይ እና ሌሎች 40 ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን ጠቅሰዋል። የወልድያን ልማት ለማምጣት አካባቢያችንን ተደራጅተን በመጠበቅ፣ አጥፊዎችን በማጋለጥ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ትግል ሕዝባችን ሊደግፈን ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ በቃሉ ወረዳ ደጋን ከተማ ተካሄደ፡፡
Next articleሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ በወረታ ከተማ ተካሂዷል፡፡