“የሩዋንዳዉ ጉብኝት ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ ጋር ያላትን ግንኙነት የሚያጠናክር ነው” ቢልለኔ ስዩም

30

ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሩዋንዳ ጉብኝት ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኀላፊ ቢልለኔ ስዩም ገልጸዋል፡፡
ቢልለኔ ስዩም የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ልዑካቸውን የሩዋንዳ ኪጋሊ የሁለት ቀናት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም ጉብኝቱ በሁለት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መኾኑን አንስተዋል፡፡ አንደኛው ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ለማድረግ ሲኾን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከ30 ዓመት በፊት በሩዋንዳ የደረሰውን የዘር ጭፍጨፋ መታሰቢያን ለመታደም ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኪጋሊ ቆይታቸውም በሩዋንዳ የግብርና ጥበቃ ኢንስቲትዩት ጉብኝት ማድረጋቸውን አብራርተዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በግብርና ምርት የተሰማሩ ተማሪዎችን ተግባራዊ ሥልጠና የሚያሠለጥን ሲሆን መልካም ተሞክሮ የሚወሰድበት እንደኾነ ነው የገለጹት፡፡ ኢትዮጵያ ለግብርና ዘርፍ እየሰጠችው ካለው ትኩረት ጋር የሚመሳሰል መኾኑን ጠቅሰው እንደአብነትም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ.ር) ተነሳሽነት ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለውን የሌማት ትሩፋት ተምሳሌት የኾኑ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡

በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ጋር በብሔራዊ ቤተመንግሥታቸው ውይይት አድርገዋል ነው ያሉት ኀላፊዋ፡፡ ባለፈው በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ላይ ሁለቱ መሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገው ነበር፡፡ ይህ ውይይትም ከዚያ የቀጠለ እንደኾነ ቢልለኔ አንስተዋል፡፡

በሁለትዮሽ ውይይታቸውም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የመከሩ ሲሆን ሀገራቱ በግብርናው ዘርፍ እያደረጉ ያሉትን ጥረቶች ወደ አህጉሪቱ መስፋት እንዳለበት ተጠቁሟል ብለዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩ የልዑካን ቡድን አባላት ደግሞ በየሥራ ዘርፋቸው ሀገራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ክንውኖች አድርገዋል ነው ያሉት፡፡

የሩዋንዳ መንግሥት በኪጋሊ ከተማ ለኢትዮጵያ ከ7 ሺህ 700 ካሬ ሜትር በላይ መሬት በመስጠት የኢትዮጵያ ኤምባሲ ማስጀመሪያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ መሪነት የመሰረተ ድንጋይ መቀመጡ ተገልጿል፡፡ ይህም የሁለቱን ሀገራት የስትራቴጂክ አጋር ስምምነት ግንኙነት የበለጠ ከፍ ያደርገዋል ተብሎ እንደሚታመን ነው ኀላፊዋ የተናገሩት፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከኪጋሊ ከተማ ከንቲባ ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችን መፈራረማቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው 30ኛ ዓመት የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ መታሰቢያ ሥነ-ሥርዓት ላይ መገኘታቸው ነው የተገለጸው፡፡

ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በመታሰቢያው ላይ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን አጋርነት አንስተዋል፤ በተለይ ከዘር ጭፍጨፋው በኋላ ኢትዮጵያ በተመድ በኩል በተዘጋጀው መልሶ የማቋቋም ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ሰላም አስከባሪ ማሰማራቷን አውስተዋል ብለዋል፡፡
ይህ የሚያሳየውም በሁለቱ ሀገራት መካከል የረጅም ጊዜ ትብብር እንደነበረ ነው ሲሉ ቢልለኔ አንስተዋል፡፡

እንደ ኤፍቢሲ ዘገባ የሁለት ቀናቱ ጉብኝትም ሀገራቱ ያላቸውን ትስስር ይበልጥ ከማጠናከር ባለፈ ለአህጉሪቱ ትሩፋት በሚኾንበት መልክ መገባደዱ ተገልጿል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ለ245 የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ ማስረከብ ተጀመረ።
Next articleሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ በቃሉ ወረዳ ደጋን ከተማ ተካሄደ፡፡