በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ለ245 የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ ማስረከብ ተጀመረ።

18

ደብረ ብርሃን: መጋቢት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከተማ አሥተዳደሩ በ2015 በጀት ዓመት ነበር በከተማው የመኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ ለማግኘት ተደራጅተው ዕውቅና ላገኙ 633 ማኅበራት ቦታ ማስረከብ የጀመረው። ዛሬ የተጀመረው ቦታ ሸንሽኖ የማስረከብ ሥራ ከ633 የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኀበራት መካከል እጣ ሳይወጣላቸው ለቆዩ ማኅበራት ነው።

በዚህ ዙር 196 መደበኛ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና 49 ልዩ ተጠቃሚ ማኅበራት በድምሩ 245 ማኅበራት ቦታ ይሰጣል ተብሏል። ለዚህም ሥራ 187 ሄክታር መሬት ከሦስተኛ ወገን ነጻ ተደርጎ መዘጋጀቱም ተገልጿል። የከተማ አሥተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በድሉ ውብሸት እንዳሉት የከተማዋን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት ቀጣይነት ያለው ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ቦታ ያገኙ ነዋሪዎች በተቀመጠው አግባብ መሠረት የመኖሪያ ቤታቸውን እንዲገነቡም አሳስበዋል። ቦታ እየተረከቡ ያገኘናቸው የከተማዋ ነዋሪዎችም በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የቦታ ባለቤት በመኾናቸው የተሰማቸውን ደስታ አጋርተውናል፡፡ ለከተማ አሥተዳደሩም ምሥጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀገራዊ ለውጡን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፍ በሰሜን ጎንደር ዞን በጠለምት እና በማይጠምሪ ከተማ ተካሂዷል።
Next article“የሩዋንዳዉ ጉብኝት ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ ጋር ያላትን ግንኙነት የሚያጠናክር ነው” ቢልለኔ ስዩም