
ደሴ: መጋቢት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ባለፉት 6 ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተከናወኑ የልማት ሥራዎች እና ሌሎች ሀገራዊ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም እውቅና የሚሰጥ እና ጽንፈኛ ኃይሎች የሚፈጽሙትን እኩይ ተግባር የሚያወግዝ ሕዝባዊ ሰልፍ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሂዷል።
የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ሙሐመድአሚን የሱፍ በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ተገኝተው መልእክት አስተላልፈዋል።
ከንቲባው በመልእክታቸው የአማራ ሕዝብ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉት ይታወቃል ብለዋል። እነዚህን ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች ለመፍታት በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር መኾን ያስፈልጋል ነው ያሉት። ጥያቄዎች መልስ የሚያገኙት ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመተባበር እንጅ በጽንፈኝነት አስተሳሰብ ሊኾን አይገባም ሲሉም አሳስበዋል።
የአማራን ሕዝብ ጥያቄዎች አስመልሳለሁ በሚል ሽፋን ጫካ የገባው ኃይል ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ወደ ንግግር ቢመጣ መንግሥት ለሰላማዊ ውይይት ዝግጁ መኾኑንም ከንቲባው አንስተዋል።
ጫካ የገባው ጽንፈኛ ኃይል የሕዝብን ጥያቄ የተሸከመ የሚያስመስል አጀንዳ ቢያራግብም ሕዝቡን ለባሰ ችግር ከመዳረግ ያለፈ የፈየደው አንዳች ተግባር እንደሌለም ተናግረዋል። ይህ ኃይል የሚፈጽመውን ግፍ ለማውገዝ ሰልፍ የወጡ የከተማዋን ነዋሪዎችም ከንቲባ መሐመድአሚን አመስግነዋል።
በሕዝባዊ ሰልፉ ላይ የተገኙ የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ባለፉት 6 ዓመታት በከተማዋ የተሠሩ የልማት ሥራዎች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መኾናቸውን ገልጸዋል። የልማት ሥራዎች የሚያስመሰግኑ እና እውቅና የሚሰጣቸው ናቸው ብለዋል።
በአማራ ሕዝብ ስም እየማሉ በክልሉ የእርስ በርስ ጦርነት እንዲባባስ የሚያደርጉ ጽንፈኛ ኃይሎች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ሲሉም የሰልፉ ተሳታፊዎች ገልጸዋል። ሰላማዊ ሰልፍ የነዚህን ኃይሎች ድብቅ አጀንዳ ለማውገዝ ያለመ መኾኑንም ጠቁመዋል።
“የሕዝቡን ሁለንተናዊ ችግሮች ለመፍታት እና የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ሰላም ያስፈልጋል” ያሉት የሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች ነፍጥ ያነገቡ ኃይሎች ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- አሊ ይመር
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!