
ደሴ፡ መጋቢት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የክልላችን አንጻራዊ ሰላም በአጭር ጊዜ ወደ ዘላቂ ሰላም እናሻግራለን፣ በጥቂት ጽንፈኛ ኃይሎች አሥተሳሰብ እኩይ ድርጊት የሚበተን ሀገር እና ሕዝብ የለም፣ ያሰበውን የሚሠራ የጀመረውን የሚጨርስ መንግሥት አለን፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የአንድነታችን እና የጥንካሬአችን ምንጭ ነው የሚሉ መልዕክቶች በድጋፍ ሰልፉ ላይ ተላልፈዋል።
ክልሉን የጦርነት ቀጣና ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ድርጊት እንቃወማለን ያሉት ሰልፈኞቹ የመጡ ለውጦችን እንደሚደግፉ እና ሰላማቸውን ለማስጠበቅ ከመንግሥት ጎን እንደሚቆሙ ተናግረዋል። በሰሜኑ ጦርነት ከተማቸው ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰበት እና በዚህም ምክንያት የሰዎች ሕይወት እንደጠፋ አስተያየታቸውን ለአሚኮ የተናገሩት የከተማዋ ነዋሪዎች ጥያቄ አለን የሚሉ ኃይሎች ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገዶች ማንሳት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
ከለውጡ በኋላ የመጡ እምርታዎችን ለማስቀጠል እንደ ፓርቲ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን የገለጹት የሀርቡ ከተማ አሥተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጀማል ኑሩ በቀጣይም የሕዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎችን ለመፍታት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የሀርቡ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ያሲን አመዴ በበኩላቸው ከተማዋን ለማሳደግ እና የሥራ ዕድል ለመፍጠር ሰላም አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል። በመኾኑም ለሀገራዊ ለውጥ እና አካታች ሥርዓት ለማምጣት ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ከንቲባው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡- ሰልሀዲን ሰይድ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!