የመገጭ ግድብ ቀጣይ እጣ ፋንታው ምንድን ነው?

87

ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የመገጭ ግድብ ከተጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በውኃ ጥም ለምትንገላታው ጎንደር እና ከግደቡ በታች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ለመስኖ አግልገሎት ይውላል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበት ነበር የግንባታ ፕሮጀክቱ የተጀመረው፡፡ ውኃን በየጊዜው የማያገኙ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች የመገጭን መጠናቀቅ በተስፋ እና በጉጉት ከጠበቁ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ መገጭ ግን በተባለው ጊዜ ሊጠናቀቅ አልቻለም፡፡

በውኃ ጥም የሚኖሩ ነዋሪዎች እና በመስኖ ለመጠቀም ተስፋ ያደረጉ አርሶ አደሮች ዛሬም በተስፋ እየጠበቁት ነው፡፡ መገጭ ግን ጉዞው አዝጋሚ ኾኗል፡፡ አሚኮ የመገጭን ግድብ የሥራ እንቅስቃሴ ተደጋጋሚ ዘገባዎች ሠርቷል፡፡ በቅርቡ በተሠራው ዜናም የክልሉ መንግሥት በሚቀጥሉት ወራት የመገጭ እድል መታወቅ አለበት፤ ለፕሮጀክቱ መጓተት በየጊዜው የሚቀያየር በርካታ ምክንያት ይቀመጣል። ወደፊት በተስፋ ለሚጠብቁት ተጠቃሚዎች ቁርጥ ያለ ነገር ማቅረብ ያስፈልጋል። የመንግሥት የመፈጸም ድክመት ማሳያ እየኾነ መቀጠል የለበትም ማለቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

መገጭን በበላይነት የሚያሠራው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትስ ምን ይላል? የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የሕዝን ግንኙነት እና ኮምዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ብዙነህ ቶልቻ በየጊዜው የሚፈጠሩ ማኅበራዊ ችግሮች፣ የተቋራጩ የአቅም ውስንነት እና ግድቡ ላይ የተፈጠረው የቴክኒክ ክፍተት ለግድቡ መዘግየት ምክንያቶች ናቸው ይላሉ፡፡

ግድቡ 77 በመቶ ከደረሰ በኋላ የቴክኒክ ችግር በማጋጠሙ ተንሸራቶ ነበር ነው ያሉት፡፡ የተንሸራተተውን ለማስተካከል ጊዜ ውስዷል ብለዋል፡፡ በየጊዜው የሚፈጠረው የፀጥታ ችግር ተቋራጩ ግብዓቶችን እንደ ልብ ለማጓጓዝ እንቅፋት መኾኑንም ነግረውናል፡፡ በችግር ውስጥ ኾኖም በሚቻለው አቅም ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ እስከ ሕዳር 30/2018 ዓ.ም ድረስ ግደቡን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ ሲሠራ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡

በእቅዱ መሠረት ለማጠናቀቅ በየዓመቱ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ ያሉት ሥራ አሥፈጻሚው የተፈጠሩ ችግሮች ግን በእቅዱ መሠረት እንዲሠራ አለማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ ከኾነ ግድቡ አሁንም ከተያዘለት የኮንትራት ጊዜ ሊያልፍ ይችላል፡፡ በመንሸራተቱ ምክንያት አፈጻጸሙ ከ77 በመቶ ወደታች መውረዱንም አስታውቀዋል፡፡ መገጭ አሁን ላይ ያለው አፈጻጸም 65 ነጥብ 8 በመቶ ነው፡፡ የሰላሙ ሁኔታ ከተስተካከለ ቢቻል በታቀደለት ጊዜ፤ ከአቅም በላይ ከኾነ ደግሞ ከእቅዱ ቢያልፍም ብዙ ባልራቀ ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የተቋራጩን አቅም ውስንነት ማሻሻል ያልተቻለው ለምንድን ነው? ካልኾነስ ውሉን አቋርጦ ለሌላ ተቋራጭ ለምንድን ነው ያልተሰጠው ? በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ ተቋራጩ ሀገር በቀል ድርጅት ነው፤ ሚኒስቴሩ ለተቋራጩ መደረግ ያለበትን ድጋፍ እያደረገ፣ የሚጠይቃቸው ነገሮች እንዲመቻቹለት፣ ንዑስ ተቋራጮቹን እንዲያስገባ እና ሥራውን እንዲያግዙት፣ ፕሮጀክቱ ቶሎ እንዲያልቅ ጫና የማሳደር እና የመደገፍ ሥራ ሠርቷል፡፡ የኮንትራት ውሉን ማቋረጥ ግን አዋጭ አይደለም ብለዋል፡፡

ምክንያቱን ሲያነሱም እስካሁን የሠራቸውን ሥራዎች ቆጥሮ መረከብ ጊዜ ይወስዳል፤ ሌላ ተቋራጭ ለማስገባት አዲስ ጨረታ ነው የሚወጣው፤ ያም የራሱን የኾነ ጊዜ ይወስዳል፤ አዲስ የሚመጣው ተቋራጭ የሥራ ዋጋው የሚጨምርበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለዋል፡፡ ሀገር በቀል፣ አንጋፋ እና በርካታ የመስኖ ፕሮጀክቶችን እየገነባ ያለ ተቋም በመኾኑ የጋራ የኾነውን ችግር ተደጋግፎ መሥራት ይሻላል ነው ያሉት፡፡

የግድቡን አፈጻጸም የበለጠ ያጓተተው የተፈጠረው መንሸራተት መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡ በግድቦች ላይ እንዲህ ዓይነት ክስተቶች እንደሚያጋጥሙም አንስተዋል፡፡ በተደጋጋሚ በዚህን ጊዜ ይጠናቀቃል እየተባለ የሚነገረው የኮንትራት ጊዜውን ታሳቢ በማድረግ ነው የሚሉት ሥራ አስፈጻሚው ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ግድቡ ላይ ምልከታ ሲያደርጉ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚገለጸው ኮንትራቱ ላይ ባለው ውል ነው እንጂ ከውሉ ውጭ መናገር አይቻልም፤ ምክንያቱም ውሉ ያስገድዳል ነው ያሉት፡፡

በተባለበት ጊዜ ያልቃል አያልቅም የሚለው ጉዳይ ግን በሥራ ሂደት የሚታወቅ ነው ይላሉ፡፡ ኮንትራቱ ላይ ያለው ጊዜ እና መሬት ያለው እውነታ ግን በእኩል ላይሄድ ይቻላል ብለዋል፡፡ ግድቡ አልቆ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች እንዲጠቀሙ እና የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች የንጹሕ መጠጥ ውኃ አገልግሎት እንዲያገኙ ይሠራል ነው ያሉት፡፡ በሕዝብ ዘንድ ለሚነሱ ጥያቄዎች ያጋጠሙ ችግሮችን እያሳወቅን ሥራውን እንቀጥላለንም ብለዋል፡፡ የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ከሕዝቡ በላይ ሚኒስቴሩን ደስተኛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡

የመገጭ ግድብ በተባለለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ከጊዜ ወደ ጊዜ የግንባታ ወጪው አሻቅቧል፡፡ ግድቡ ወደ ሥራ ሲገባ 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ውል ተይዞለት ነበር፡፡ አሁን ላይ ያለው ግን 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ግድቡ በተባለለት ጊዜ ካልተቋጨ ከዚህ በላይ ሊሄድ እንደሚችልም ይጠበቃል፡፡

የግድቡ የወደፊት እጣ ፈንታ ምንድን ነው? ተብሎ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ሥራው ተጠናቅቆ፣ በዚያ አካበቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች ምርት እና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ፣ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሃብት የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ፣ ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚኾን ምርት እንዲመረት፣ የጎንደር እና አካባቢዋ ነዋሪዎች የንጹሕ መጠጥ ውኃ ተጠቃሚ እንዲኾኑ ያደርጋል፤ ማለቁ አይቀርም፤ የጊዜ ጉዳይ ነው፣ ሁኔታዎች ወደ መደበኛው እንቅስቃሴ ተመልሰው እንደ ልብ ተራሮጦ መሥራት የሚቻልበት እድል ከተፈጠረ ለሥራው በጊዜ መጠናቀቅ የተሻለ ይኾናል ብለዋል፡፡

እንደ አሠሪ ተቋም ተቋራጩ ላይ ተጽዕኖ የማድረግ፣ የሚያስፈልገውን ድጋፍ የማድረግ ሥራ እንሠራለን ነው ያሉት፡፡ እንደሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ ትኩረት ከተሰጣቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንደኛው ነው፤ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ይጠናቃቃል በተባለበት ጊዜ ማጠናቀቅ አልተቻለም።
አሁንም ባለው አቅም እና ሁኔታዎች በፈቀዱ መጠን ሥራው እየተሠራ ነው፤ እስካዛሬ ድረስ በትዕግሥት የጠበቀው ሕዝብ አሁንም ተጠናቅቆ እስኪረከብ ድረስ በትዕግሥት እንዲጠብቅ አደራ እላለሁ ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዥረቱ የሚፈስሰው ትውልድ!
Next articleበሰቆጣ ከተማ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።