
ባሕር ዳር: መጋቢት 30/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ትውልድ ዥረት ነው፤ አንዱ ሲሄድ ሌላኛው የሚከተል፤ የማያቋርጥ የማይቆም ፍሰት። እየጨመረ የሚሄድ፤ መነሻው እንጂ መዳረሻው የማይበየን። በዚህ የዥረት ጉዞው እየጎሸ እየጠራ፤ እየፈጠነ፣ እያዘገመ፤ በአርምሞ፤ ለሣር ለምድሩ ተመችቶ ወይ ደግሞ በደራሽ ጎርፍ እና ፏፏቴው ከአለት ጋር እያላጋ ይጓዛል። የሰው ልጅ ህይወትም እንደ ዥረት ነው። ተያያዥ፣ የማይቆም፣ ቀጣይ እና መሪና ተከታይ ኾኖ የሚጓዝ።
ሰዎች ትውልድን የዚያ ወይም የዚህኛው ዘመን በማለት በሥርዓተ መንግሥት ሊበይኑት ይሞክራሉ። ለምሳሌ የኃይለሥላሴውን ዘመን በቀድሞነቱ እና በበጎነቱ፤ የደርጉን እና ወዲህ ያለውን ዘመን በብልሽቱ ሲፈርጁ እና ሲያነጻጸሩ ይታያሉ፡፡ ነገር ግን በየሥርዓተ መንግሥታቱ መካከልም አገናኝ ድልድይ ትውልድ እና እሴት መኖሩን ልብይሏል። የሌሊቱ ጨለማ በአንዴ ጠፍቶ የቀኑ ብርሃን ቦግ! እንደማይል ሁሉ የትውልድ ልማትና ጥፋቶች፣ ምቾት እና ጉርብጥና፣ ሥልጣኔ እና ድንቁርና፣ ትኅትናና ብልጽግና ወዘተ ቶሎ ቶሎ የሚቀያየሩ አይደሉም።
ዛሬ ላይ የሚተቸው የትውልዱ የሥነ ምግባር ብልሽት ዛሬ ተፈጥሮ፣ ዛሬውኑ የገነገነ አይደለም። የትላንቱ ለዛሬው የዛሬው ለነገው እያለ በሰንሰለታዊ ትስስር በዥረታዊ ጉዞ እዚህ የደረሰ እንጂ። በሥርዓተ መንግሥታት ለውጥ የመስፈር ባሕል ስላለን እንጂ በሕዝብ ውስጥ ያለ መልካምም ኾነ መጥፎ እሴት ከሕዝቡ የዥረት ጉዞ ጋር አብሮ የሚኖር እና የሚጓዝ ነው።
ድሮ ድሮ ወድቆ የተገኘን እቃ ”እቃ የጠፋሽ…” በማለት ለባለቤቱ እንደሚሰጥ እንሰማለን፤ ዛሬ ዛሬ ደግሞ አስገድዶ የመቀማት ጊዜ ላይ እንገኛለን። በመካከላቸውም ካላዩኝ እሰርቅ፤ ካዩኝ እስቅ’ ዓይነት ድልድይ የኾነ ሥነ ምግባር ያለው ትውልድ መኖሩንም አንርሳ፡፡ በእያንዳንዱም መካከል ሌሎች ድልድዮች አሉ።
የሥነ ምግባርን ብልሽት በሃይማኖት፣ በባሕል፣ በሞራል እና በሕግ እየገሩ ከመሄድ በስተቀር ከትውልድ ፍሰት ጋር አብሮ መጓዙና መስፋፋቱ አይቀሬ ነው። የትላንቱን ቀድሶ የዛሬውን አርክሶ ለማለፍ መሞከርም የትም አያደርሰንም። በየጊዜው የምንሰማቸው እና የምናያቸው የትውልዱ ”መበላሸት” ተብለው የሚፈረጁትን ሥነ ምግባሮች ራሱ ”ትውልዱ” ደግሞ ሥልጣኔ፣ አራዳነት፣ ፈጣንነት ወይም ጉብዝና አድርጎ ሊገነዘባቸው ይችላል። በአንድ ዘመን ላይ ኾነን እንኳ ነገሮችን የምንገነዘብበት እና የሥነ ምግባር ብያኔ የምንሰጥበት ልዩነት መኖሩን ስናይ መጥፎም ኾነ ጥሩ ነገሮች እንደ ዥረት የሚፈስሱ እንጂ ከአንደኛው ያሉ ከሌላኛው የሌሉ አድርገን ለመደምደም ያስቸግረናል።
በእርግጥ በትውልድ ውስጥ ያሉ ልማቶችም ኾኑ ጥፋቶች ተሰናስለው እየተመጋገቡ የሚፈስሱ እንጂ በአንዴ የማይፈጠሩ ወይም የማይጠፉ መኾናቸውን እንገነዘባለን። እኛ የትላንቱን የማድነቅ፣ የዛሬውን የመናቅ፣ የነገውን የመናፈቅ ልማድ ካልተጠናወተን በስተቀር ዛሬ ለምንንቀውም ኾነ ነገ ለምንናፍቀው ነገር የትላንት እና የዛሬ እርሾ ያለበት መኾኑን ማወቅ ያስፈልጋል። አውቆም ለጎጂው ማስተካከያ ለጠቃሚው ማጠናከሪያ መሥራት የዛሬዎቹ ኀላፊነት ነው።
የሥነ ዜጋ እና የሥነምግባር ትምህርት በሚሰጥባት፣ የሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና አዋጅ እና ተቋም፣ መልካም ስብዕናን አስተምረው የሚቀርጹ የሃይማኖት ተቋማት ባሉባት ሀገር ከጊዜ ጊዜ ሥነ ምግባር እየሸሸ፣ ግብረ ገብነት እየተበላሸ፣ ራስ ወዳድነት እና ስግብግብነት እየተስፋፋ መተሳሰብ እየጠፋ ይታያል። ለዚህ ምክንያቱ ”የዘመኑ ትውልድን” ተጠያቂ የሚያደርጉ በርካቶች ናቸው። ነገር ግን ”የዘመኑ ትውልድ” ከየት ተፈጠረ? ለዚህ ያደረሰውስ ማን ነው? የዛሬው ትውልድ ”ከትላንቱ” የወጣ አይደለም ወይ? ለዛሬው ብልሽት የምናደንቀው ትላንት ድርሻ የለውም ወይ? ማለት ያስፈልጋል፡፡
ትላንት ተወልደን በሥነ ምግባር ታንጸን ኖርን የምንለውስ ለዛሬ ልጆቻችን ምን አስተማርን? ምን አቆየን? የሌላውን ልጅ ሥነ ምግባር የሌለው አድርገን ለመፈረጅ የሚቀናን ሲኾን የኔ ልጅስ ብለን ለማሰብ ግን እንቸገራለን። ይህ ችግርን በሌላው የማላከክ አባዜ በትውልድ ቀረጻው ላይም ይስተዋልብናል።
የአሁኑ ትውልድ በተለይም ወጣቱ በኑሮ ውድነት፣ በቴክኖሎጂ መዘመን እንዲሁም በምዕራባውያን የባሕል ወረራ ምክንያት ”ድሮ” ብለን በምንጠራው ዘመን የነበረውን ትውልድ ሥነ ምግባር እና ስብዕና ይዞ ሊገኝ አይችልም። የዛኔው ትውልድም ዛሬ ላይ ያሉት ከባቢያዊ ሁኔታዎች ቢኖሩት ኖሮ የዛሬውን ዓይነት ሥነ ምግባር ላለመያዙ ዋስትና የለንም።
ቴክኖሎጂን ይለማመድ ብሎ ታብሌት ገዝቶ የሰጠ ወላጅ ልጁ የጌም ሱስ ቢይዘው እና ቤተሰባዊ እና ማኅበራዊ ግንኙነቱ ቢበላሽ ”በዘመኑ ትውልድ” ተፈርጆ ሊጠየቅ ነው? በሀገር ባሕል የተሠራ ሸማን ”በኋላቀርነት” ንቆ ሱፍ በክራባት የሚለብስ አባት የተቦጫጨቀ ሱሪ የሚለብስ ልጁን ”በዘመኑ ትውልድነት” ፈርጆ ለመውቀስ ምን ሞራል ይኖረዋል? የራሱን ትቶ ሌላውን ለመኾን ቀድሞ የጀመረው አባት ወይስ ልጅ? ያለ አበርክቶው የሚጠቀም እና ”ምን ይደረግ ዘመኑ የሚጠይቀው ነው” እያለ የራሱን ጥፋት ጤነኛ የሚያደርግ ጎልማሳ ወጣቱ በትህትና አገልጋይ ብቻ እንዲኾን መጠበቅም የለበትም።
የዘመኑ ብለን የምንጠራው ትውልድ እና አንዳንድ ጎጂ ሥነ ምግባሮች መጤ ብቻ ሳይኾኑ ከኛው ተፈጥረው ያደጉ መኾናቸውንም ማስተዋል ለመፍትሄው የጋት ያክልም ቢኾን ያስሄዳል። ገዳይነትን የሚያሞግሱ ዘፈኖች የባሕላችን መገለጫዎች በኾኑበት ሀገር ዛሬ ላይ ለሃብት ሲባል የሚታየውን መካካድ እና መገዳደል ትውልዱን ተወቃሽ ልናደርግበት አንችልም። ”ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” ይሉት ሥነ ቃልም የድሮ ነው፡፡ ሌላም ሌላም።
ዛሬ ብለን በምንጠራው ግልጽ ደንበር በሌለው ጊዜ ላይ የሚስተዋለው ”በትውልዱ” የሚሳበበው የሥነ ምግባር ችግር በጊዜ ሠንሠለት፣ በትውልድ ዥረት ሲመጋገብ የመጣ፣ ቀድሞ ተፈጥሮ ያደገ እንጂ በአንድ ጀንበር እንደተፈጠረ ”ለዛሬው ትውልድ” ብቻ የምንሰጠው ጥፋት አይደለም። ከትላንት ዛሬ፤ ከዛሬው ነገ እየባሰ መኾኑን እያየነው ”የትላንት” ብለን የፈረጅነውን ትውልድ ከመውቀስ ለነገው ምን ይጠበቃል? ምን ማሰብና ማድረግ አለብን፡፡
ልጆቻችንን እድሜያቸው በሚፈቅደው ልክ በሥነ ምግባር ታንጸው እና በዕውቀት በልጽገው እንዲያድጉ ማድረግ ያስፈልጋል። ከራሳቸው አልፈው ሌላውና የሀገር ጉዳይ ግድ የሚላቸው አድርጎ መቅረጽ ያስፈልገናል፡፡ ከውድድር ይልቅ ትብብርን ልናሰርጽላቸው ይጠበቅብናል፡፡ ያለ አበርክቶው የሚያገኘውን ጥቅም ከየት አመጣኸው ብሎ ያልጠየቀ ወላጅ ”ትውልዱን” በጅምላ ሊተች አይገባውም።
በትላንት እና በነገው መካከል ያለው የዛሬው ትውልድ አላግባብ ትላንትን ከማድነቅ፣ ዛሬን ከመናቅ እና ነገን ከመናፈቅ ወጥቶ ለጥፋቱም ለልማቱም ጊዜውም፣ ትውልዱም፣ ዓለም አቀፍ መሥተጋብሩም ድርሻ እንዳላቸው መገንዘብ ይገባል። ይልቁንም በሂደቱ አወንታዊ አስተዋጽኦ ለማበርከት እና አሻራን ለማኖር በተናጠልም ኾነ እንደማኅበረሰብ መሥራት ይገባናል። ዛሬ ላይ አለ የምንለው ”የትውልድ ዝቅጠት” ነገ የባሰ እንዳይኾን ዛሬ በተናጠልም በጋራም የትውልድ ግንባታ ሥራዎችን መሥራት ይጠይቀናል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!