ተገማች ያልኾነ የግንባታ ዕቃዎች የዋጋ ጭማሪ እና የጸጥታ ችግር የጤና ፕሮጀክቶች እንዳይጠናቀቁ እንቅፋት መኾኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ።

31

ደሴ: መጋቢት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጤና ፕሮጀክቶች የግንባታ ውል አሥተዳደር እና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር በኮምቦልቻ ከተማ ምክክር አካሂዷል።

በምክክር መድረኩ የምሥራቅ አማራ ዞኖች እና የከተማ አሥተዳደር የጤና መምሪያ ኀላፊዎች እና ከተለያዩ ቦታዎች የተውጣጡ የፍትሕ አካላት ተገኝተዋል። ተገማች ያልኾነ የግንባታ እቃዎች መጨመር፣ የተቋራጮች የአፈጻጸም ችግር እና በተለይ ደግሞ ክልሉ ያለበት የጸጥታ ችግር እንዲሁም የፋይናንስ እጥረት በዋናነት በዘርፉ የሚሰተዋሉ ችግሮች መኾናቸው በምክክር መድረኩ ተነስቷል።

በቀጣይ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ መኾኑ ተገልጿል። አሚኮ ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች ከፕሮጀክቶች ግንባታ ጋር በተያያዘ ተቋራጮች በውሉ መሠረት በወቅቱ ያለማጠናቀቅ፤ በክልሉ ያለው ስር የሰደደ የፋይናንስ እጥረት ብሎም በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ፕሮጀክቶችን በወቅቱ በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዳይሰጡ ፈተና ስለመኾናቸው ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኀላፊ ገስጥ ጥላሁን በክልሉ በግንባታ ላይ ባሉ የጤና ፕሮጀክቶች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍተኛ በመሆኑን ገልጸዋል። ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተከታታይ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት ለችግሮቹ መቀረፍ እንደሚሠራም ተናግረዋል።

የጸጥታ ችግር፤ ተቋራጮች በወሰዱት ውል መሠረት ሠርተው ያለማጠናቀቅ እንዲሁም የገንዘብ እጥረት በግንባታ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት እንዳይሆኑ ማድረጋቸው በውይይት መድረኩ ተነስቷል።

ችግሮችን ለመቅረፍ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት በመሥራት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉም ምክትል ቢሮ ኀላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- ደምስ አረጋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሁለተኛው ዙር ሠልጣኞች መመረቅ የሰላም ግንባታ ትግሉን የበለጠ ውጤታማ ያደርገዋል” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)
Next article“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሩዋንዳን ከችግር ለመታደግ አግዘዋል” ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሚ