“የሁለተኛው ዙር ሠልጣኞች መመረቅ የሰላም ግንባታ ትግሉን የበለጠ ውጤታማ ያደርገዋል” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)

107

ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ሁለተኛ ዙር ሠልጣኞች በብርሸለቆ የውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተሐድሶ ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው ተመርቀዋል።

በምርቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ እና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው፣ የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጦር መኮንኖች ተገኝተዋል።

በሥነ ሥርዓቱ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) “ከሀገራችሁ እና ከሕዝባችሁ አደራ ለመቀበል በቅታችኋል እና እንኳን ደስ አላችሁ” ብለዋቸዋል ተመራቂዎችን። የአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በርካታ ውስብስብ ችግሮችን አልፎ በጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች ብርቱ ተጋድሎ ሕዝባችን የሰላም አየር መተፈንስ እንዲችል ኾኗል ነው ያሉት።

አማራ ክልል የተረጋጋ ሰላም እንዳያገኝ እያደረገ ያለው ጽንፈኛ ቡድን ሕዝብን ወደ ቁልቁለት ጉዞ እንዲሄድ እያደረገ መኾኑን ገልጸዋል። በሕዝብ ይሁንታ የተመረጠውን መንግሥት በኃይል በመጣል የራሱን ፍላጎት ለመጫን ያለ የሌለውን ኃይል አሟጦ በርካታ ውድመቶችን እየፈጸመ ነው ብለዋል። የክልሉ ሕዝብ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ እንቅፋት ፈጥሮበታል ነው ያሉት። ማዳበሪያ፣ የሕክምና ቁሳቁስ እና የእርዳታ እህል ወደ ኅብረተሰቡ እንዳይደርስ ጥሯል፤ ዘርፏልም ብለዋል። የክልሉ ኢንቨስትመንት ተጎድቶ የሥራ አጥ ቁጥር እንዲሰፋ ማድረጉንም ገልጸዋል።

ሕጻናት ተረጋግተው እንዳይማሩ በየቦታው ቦምብ በማፈንዳት የአካል ጉዳት እና በሥነ ልቦና ችግር እያደረሰ መኾኑንም ተናግረዋል። ይህ ቡድን አማራን የሚጎዳ እና ለማጎሳቆል የቆመ ነው፤ ሕዝባችሁን ለመታደግ ታሪክ የሚሠራበት ወቅት በመኾኑ ለታሪክ ራሳችሁን በጀግንነት እና በቆራጥነት ዝግጁ ማድረግ አለባችሁ ብለዋል። ሕዝብን የመታደግ አደራ እንደተጣለባቸውም አሳስበዋል።

ክልሉ ሰላም አንዲኾን መንግሥት የሰላም ጥሪዎችን ማስተላለፉን ያስታወሱት ኃላፊው የሰላም አማራጮች አሁንም ከፍት መኾናቸውን ነው የገለጹት። የሰላም አማራጮችን የማይቀበሉ አካላት አሁንም ሕዝብን ለእንግልት እየዳረጉት ነው ብለዋል። ከሰላም ጎን ለጎን ሕግ የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የተናገሩት ኀላፊው በርካታ አካባቢዎች ከጸጥታ ችግር ነጻ ኾነዋል ነው ያሉት። በመጀመሪያው ዙር የሠለጠኑ የቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ሕዝባቸውን እየካሱት መኾናቸውንም አስታውቀዋል። በታሪክ ተመዝግቦ የሚቀመጥ ሥራ እየሠሩ መኾናቸውንም ተናግረዋል። “የሁለተኛው ዙር ሠልጣኞች መመረቅ የሰላም ግንባታ ትግሉን የበለጠ ውጤታማ ያደርገዋል፤ የሕዝባችን የሰላም ተስፋም ያለመልመዋል” ነው ያሉት።

ቢሮ ኀላፊው በቀጣይም መሰል ሥልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት። ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ጠንካራ ሕግ የማስከበር ሥራ በመሥራት አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እናከናውናለን ብለዋል። የተጀመረው ሕግ የማስከበር ዘመቻ በውጤታማነት እንዲጠናቀቅ ኅብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን ተሰልፎ የጽንፈኛ ቡድኑን አውዳሚ ተግባሮች ማውገዝ እና ማጋለጥ ይገባዋል ነው ያሉት።

አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም በመትከል ክልሉ በልማት ተጠቃሚ እንዲሆን የማይተካ ሚና እንዲወጡም አደራ ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጉድለቶችን በማረም እና በማስተካከል ዳግም ቃል ገብታችሁ ለሕዝብ፣ ለመንግሥት እና ለተቋማችሁ ታማኝ ኾናችሁ ልትሠሩ ይገባል” ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን
Next articleተገማች ያልኾነ የግንባታ ዕቃዎች የዋጋ ጭማሪ እና የጸጥታ ችግር የጤና ፕሮጀክቶች እንዳይጠናቀቁ እንቅፋት መኾኑን የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ገለጸ።