“ጉድለቶችን በማረም እና በማስተካከል ዳግም ቃል ገብታችሁ ለሕዝብ፣ ለመንግሥት እና ለተቋማችሁ ታማኝ ኾናችሁ ልትሠሩ ይገባል” ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን

73

ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት በብርሸለቆ የወታደራዊ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተሐድሶ ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው ተመርቀዋል። በሁለተኛው ዙር የተሐድሶ ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው የተመረቁ የቀድሞው የልዩ ኃይል አባላት ሕዝብን ለመካስ ቁርጠኛ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ረዳት ኢንስፔክተር ከድር ሁሴን በወታደራዊ ማሠልጠኛ ተቋሙ ብዙ አቅም ማግኘታቸውን ተናግሯል። የክልሉ የፖለቲካ መሪዎች የክልሉን ነባራዊ ሁኔታ እና ሕዝቡን ከገባበት ችግር ለማውጣት የሚሠራውን ሥራ በተመለከተ በቂ ግንዛቤ እንደሰጧቸውም ገልጿል። ያገኙት ትምህርት ለቀጣይ ግዳጅ የሚያነሳሳ መኾኑንም ተናግሯል። ተጸጽተን ሕዝባችን ለመታደግ ዝግጁ ነንም ብሏል። በሞራል፣ በወኔ፣ በአጭር ጊዜ ሕዝባችንን እንታደግ እያሉ መኾናቸውንም አመላክቷል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከአማራ ክልል የጸጥታ አካላት ጋር በመኾን በወታደራዊ ማሠልጠኛ ተቋሙ ጥሩ ትምህርት እንደሰጣቸውም ገልጿል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት መስዋዕትነት እየከፈለ፣ ሕዝብን እየታደገ መኾኑንም ተናግሯል። ጽንፈኞች ሕዝብን ለማወናበድ የሚሠሩት ሥራ አስቀያሚ ነገር መኾኑን መገንዘቡንም ገልጿል።

የጽንፈኛውን ውስጣዊ ሥራ እናውቀዋለን ያለው ረዳት ኢንስፔክተር ከድር በወታደራዊ ማሠልጠኛው የተገኘውን አቅም ተጠቅመን ፣ ሕዝብ እንዳይታለል በማድረግ ሕዝብ እና መንግሥት የሰጠንን አደራ እንወጣለን ነው ያለው።

እኛ እንደ ክልል ሳይኾን እንደ ኢትዮጵያ ነው የምናስበው፣ ሕዝባችን በድለናል፣ አሁን ተቆጭተን ከመከላከያ ሠራዊት እና ከሕዝባችን ጋር ኾነን ከክልሉ አልፈን ሌሎች አካባቢዎች ላይ ሰላም እናስከብራለን ብሏል። “የሕዝባችንን እንባ ለማበስ ዝግጁ ነን፣ በተሰጠን ግዳጅ መሠረት በአጭር ጊዜ ክልሉ ወደ ልማት እንዲገባ ቁርጠኞች ነን” ሲልም ተናግሯል። የክልሉ ሕዝብ ዘራፊውን ቡድን ለማስወገድ በሚደረገው ተጋድሎ ከጎናቸው እንዲሰልፍም ጥሪ አቅርቧል። ክልሉን ከእኛ ውጭ የሚታደግልን የለም፣በአጭር ጊዜ ወደ ሰላም እንመልሰዋለን ነው ያለው።

ሌላኛዋ ሠልጣኝ ኮንስታብል ብርቱካን ዛፌ በሥልጠናው ጠቃሚ ነገሮችን ማግኘታቸውን ተናግራለች። “ለክልሉ የምንቆም መኾናችንን እናረጋግጣለን” ነው ያለችው። ከጽንፈኝነት የወጣ አስተሳሰብ በመያዝ ለክልሉ ሕዝብ ለመቆም ቁርጠኛ እንድንሆን የሚያደርግ ሥልጠና ተሰጥቶናል ብላለች።

ዋና ሳጅን ትዕግሥት ዓለሙ የሥልጠና ቆይታቸው ጥሩ እንደነበር ነው የተናገረችው። በክልሉ ያለውን የሰላም እጦት በዘላቂነት ለመቀልበስ በቁርጠኝነት እንደሚሠሩም ገልጻለች። የክልሉን ሰላምም እናረጋግጣለን ብላለች።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን የቀድሞ ልዩ ሀይል አባላትን መልሶ ለማደራጀት በተሠራው ሥራ ኾነ ተብሎ በወጣ ሐሰተኛ መረጃ ዓባላቱ የአደረጃጀቱ ተጠቃሚ ሳይኾኑ መቅረታቸውን አስታውሰዋል። “በሰሜኑ ጦርነት አኩሪ ገደል የፈጸሙት የልዩ ኃይል አባላት በአደረጃጀቱ ተጠቃሚ ሳይኾኑ፣ እቅዱም ሳይሰካ፣ በሐሰተኛ ቅስቀሳ ሠራዊቱ ወደ ቤቱ እንዲመለስ እና አኩሪ ገድሉን ወደኋላ እንዲመልስ አድርጓታል” ነው ያሉት።

በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተሳታፊ ባለመኾን ራሳቸውን ጠብቀው በመቆየት እና መንግሥት ባደረገው ጥሪ መሠረት የተሐድሶ ሠልጣኝ ተመራቂዎች ለመኾን መብቃታቸውንም ገልጸዋል።

አደረጃጀቱ በአግባቡ ባለመፈጸሙ በአባሎች እና በአካባቢው የጸጥታ ችግር አጋጥሟል ነው ያሉት። አብዛኛው ሠራዊት ራሱን ጠብቆ በመቆየቱ ሥልጠናውን ወስዶ ለቀጣይ ግዳጅ ዝግጁ ኾኗል ብለዋል። ክልሉ በሰሜኑ ጦርነት ከደረሰበት ጉዳት ሳያገግም በውስጡ በተፈጠሩ ጽንፈኛ ዘራፊዎች ምክንያት በሰው ሕይወት፣ በንብረት እና በመሠረተ ልማት አውታሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ነው ያሉት።

በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሰላማችን ተስተጓጉሏል፣ የተጀመሩ ልማቶች ተጠናክረው እንዳይቀጥሉ አድርጓል ያሉት ኮሚሽነሩ የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይሎች እየከፈሉት ባለው መስዋዕትነት የክልሉ ሰላም መሻሻል አምጥቷል ብለዋል።

ፖሊስ ለሙያው ታማኝ፣ ቁርጠኛ፣ ገለልተኛ፣ ለሙያ ግዴታው ተገዢ፣ ሕዝብን በመልካም ሥነ ምግባር የሚያገለግል፣ በሕግ የተመረጠ መንግሥትን የሚያከብር፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ፍፁም ነጻ ኾኖ በሥልጣን የተሰጠውን ሕግ የማስከበር ሥራ የሚሠራ፣ ወንጀልን የሚከላከል፣ ኅብረተሰብን ከዘራፊ የሚጠብቅ ታማኝ ነው ብለዋል።

ፖሊስ ሕግን በማክበር እና በማስከበር የዜጎችን ሰላም በመጠበቅ በፍትሕ ሥርዓቱ የማይተካ ሚና እንዳለውም ተናግረዋል። “እውቀታችሁን፣ ልምድ እና ችሎታችሁን በመጠቀም የበለጠ በሥራ ላይ እያዳበራችሁት እንደምትቀጥሉ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ” ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

“ጉድለቶችን በማረም እና በማስተካከል ዳግም ቃል ገብታችሁ ለሕዝብ፣ ለመንግሥት እና ለተቋማችሁ ታማኝ ኾናችሁ ልትሠሩ ይገባል” ብለዋቸዋል። “ከጽንፈኛ አስተሳሰብ፣ ከሙያ ሥነ ምግባር ብልሽት፣ ከክህደት፣ ከሀብት እና ንብረት ብክነት ራሳችሁን መጠበቅ እና ስህተት ሲያጋጥም ወዲያውኑ በማረም በሕግ ተመስርታችሁ የሚሰጣችሁን ተግባር ብቻ እንድትፈጽሙ አሳሳስበላሁ” ሲሉም አስገንዝበዋል።

ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከክልሉ የጸጥታ ኃይሎች፣ ከአሥተዳደር መዋቅሩ እና ከሕዝቡ ጋር ራሳችሁን አጠናክራችሁ እንደምትሠሩ እተማመንባችለሁ ነው ያሉት። ለሥልጠናው መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ጽንፈኝነት እያደገ ሲመጣ ራስን ይበላል” አቶ ደሳለኝ ጣሰው
Next article“የሁለተኛው ዙር ሠልጣኞች መመረቅ የሰላም ግንባታ ትግሉን የበለጠ ውጤታማ ያደርገዋል” መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር)