
ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ የቀድሞው የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ሁለተኛ ዙር ሠልጣኞች በብርሸለቆ የውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የተሐድሶ ሥልጠናቸውን አጠናቅቀው ተመርቀዋል።
በምርቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አስተባባሪ እና የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው፣ የአማራ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጦር መኮንኖች ተገኝተዋል።
አቶ ደሳለኝ ኢትዮጵያ በፈተና እና በተስፋ ተቃርኖ ውስጥ መኾኗን አንስተዋል። ባለፉት ዓመታት በርከት ያሉ የልዩነት አስተሳሰቦች መገንባታቸውን የተናገሩት አቶ ደሳለኝ ጥላቻ እና ጥርጣሬ ነግሶ የሕዝቦች አንድነት ተሸርሽሮ ቆይቷል ነው ያሉት። ልዩነት ካለ አንድነት የለም፣ አንድነት ከሌለ ጽንፈኝነት መፈጠሩ ግድ ነው ብለዋል።
ቢሮ ኀላፊው “ጽንፈኝነት እያደገ ሲመጣ ራስን ይበላል” ነው ያሉት። ከለውጥ በኋላ “የእኔ ሀሳብ የበላይነት ካልኾነ” የሚል አካል እየተፈጠረ መምጣቱን ገልጸዋል። የኔ ሀሰብ ብቻ ይሰማ የሚሉ አካላት የሚፈጥሩት ጦርነት የአማራ ክልልን በእጅጉ ጎድቷል ብለዋል። በክልሉ ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት በመመከት በኩል የቀድሞ ልዩ ኃይል አባላት ታሪክ የማይረሳው አሻራ ማሳረፋቸውንም ገልጸዋል።
አንድ ጠንካራ ኃይል ለመፍጠር በማሰብ በመልሶ ማደራጀት የተደረገው ጥረት በሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ተጠልፎ አባላቱን መበተኑን አስታውሰዋል። ሕዝቡ ከሰሜኑ ጦርነት ቁስል ሳይሽር በራሱ ልጆች መወጋቱንም ተናግረዋል። ጽንፈኛው ኃይል የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ያለ ስሙ ስም ሰጥቷል፣ የሕዝብ መገልገያ መሠረተ ልማቶችን እና ሰብዓዊ ሃብቶችን አውድሟል ነው ያሉት። አሁን ላይ ከሽምቅ ውጊያ ወደ ሽብር መውረዱንም አስታውቀዋል።
ሕዝብ እንዲሸበር፣ ተስፋ እንዳይኖረው፣ ወደ ልማት እንዳይገባ እና የሕዝብ ጠላት የኾኑ ኃይሎችን ጎትቶ እየሠራ ያለ፣ ከእኛ የተወለደ፣ የእኛ ያልኾነ ባንዳ ነው ብለዋል። የልዩ ኃይሉን አባላት ከማፍረስ አልፎ ጀብዱን እና ታሪኮችን በመቀማት የድርጊት ተሳታፊ ለማድረግ መሞከሩንም ገልጸዋል። ጽንፈኝነት እና አክራሪ ብሔርተኝነት ከፋፋይ፣ ራስን የሚበላ፣ አደገኛ በሽታ መኾኑን ከእኛ በላይ ማንም ሊረደው አይችልም ብለዋል።
የአማራን ሕዝብ ከትልቅነት ለማውረድ ሙከራ ያደረገ ታሪካዊ እጥፋት እንደገጠመውም አንስተዋል። ይሄን ታሪክ ወደ ተስፋ እና ድል የመቀየር ኃላፊነት በእኛ ላይ ወድቋል ነው ያሉት። ሕዝቡ የምጣኔ ሀብት እና የሰላም ተጠቃሚነት እንዲኖረው፣ አምራች ዜጋ እንዲፈጠር የማድረግ ታሪካዊ አደራ በእናንተ ላይ ወድቋል ብለዋቸዋል ሠልጣኞችን። “ከራስ በላይ ለሕዝብ ራሱን የሚሰጥ፣ የዓላማ ጽናት እና የተግባር አንድነት ያለው፣ ከፖለቲካ እና ከሃይማኖት ውግንና የጸዳ፣ ለሕግ የበላይነት መከበር የሚጸና፣ ሕዝብ የመረጠውን መንግሥት የሚያከበር፣ የሚታመን፣ ወታደራዊ የዕዝ ሰንሰለት የሚያከብር ሠራዊት ኾናችሁ የክልሉን ተስፋ እንደምታለመልሙ አልጠራጠርም” ነው ያሉት አቶ ደሳለኝ።
የክልሉን ሕዝብ የውጭ እና የውስጥ ተጋላጭነቱን የመቀነስ አደራ እንዳለባቸውም አስገንዘበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!