
ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በሩዋንዳ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ መንግሥት ለኢትዮጵያ ኤምባሲ ጽሕፈት ቤት መገንቢያ ባስረከበው 7 ሺ 7 መቶ 71 ካሬ መሬት ላይ ነው የመሰረት ድንጋዩ የተቀመጠው።
የመሰረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ለኢትዮጵያ ኤምባሲ በኪጋሊ የተበረከው መሬት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ፍሬያማ እንዲኾን የሚረዳ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያም ለሩዋንዳ ኤምባሲ መገንቢያ በአዲስ አበባ እኩል መጠን ያለው መሬት መስጠቷን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያና በሩዋንዳ መካከል እ.ኤ.አ ከ2012 ጀምሮ 23 ስምምነቶች እና የመግባቢያ ሰነዶች ተፈርመዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ እንደገለጹት እነዚህን በተሻለ ወደ ውጤት ለማስገባት የኢምባሲ ጽሕፈት ቤት ግንባታ ቁልፍ ሚና አለው።
ሁለቱ ሀገራት ከሁለትዮሽ ግንኙነት ባለፈ በዓለም አቀፍ የትብብር መድረኮች አቋማቸውን በኅብረት የሚያራምዱ እንደኾነም አንስተዋል።
ሩዋንዳ ከቅኝ ግዛት ለመውጣት ባደረገችው ተጋድሎ ወቅትም ኾነ ከአስከፊው ዘር ጭፍጨፋ በኋላ ኢትዮጵያ ቀድማ በመድረስ ለሩዋንዳውያን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጓ ይታወሳል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!