በግድቡ ኢትዮጵያ ያካበተችው ልምድ እና የዲፕሎማሲ ችሎታ በቀጣይ በሚገነቡ ሌሎች ግድቦች ሊገጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን ለማለፍ እገዛ እንደሚያደርግ የውኃ ፖለቲካ ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ.ር) ተናገሩ፡፡

16

ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ.ር) እንደገለጹት መላው ኢትዮጵያውያን የግድቡ ግንባታ ከጀመረበት ወቅት አንስቶ በገንዘብ እና በሀሳብ ሲደግፉ ቆይተዋል፡፡ ይህም ባለፉት 13 ዓመታት የግድቡ ግንባታ እንዲቆም ሲደረግ የነበረውን ከባድ ጫና ተቋቁሞ ለማለፍ ትልቅ ጉልበት ኾኗል፡፡

በዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ በዓለም አቀፍ ሕግ፣ በውኃ እንዲሁም በግድብ አሠራር የተካኑ ተመራማሪዎች በመመካከር እና በድርድር በመሳተፍ ትልቅ አስተዋፅዖ አድርገናል ያሉት ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ.ር)፤ መንግሥትም በቁርጠኝነት በግድቡ የግንባታ ሂደት የነበረውን ጫና ለመወጣት ትልቅ ኃይል እንደፈጠረለት አመልክተዋል፡፡

እንደ ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ.ር) ገለጻ በቀጣይም በግድቡ ላይ የሚደረገው ጫና ሙሉ ለሙሉ ሊቆም አይችልም፡፡ የዓባይ ግድብ የኃይል ማመንጫ ግድብ በመኾኑ ውኃው የሚደርስባቸው ሀገራት ሁሉ ቅሬታ ፈጥሮባቸው ነበር፡፡ በተከታታይ በተደረጉ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ቅሬታ የነበረባቸውን ማሳመን ተችሏል፡፡

በታላቁ ዓባይ ግድብ ኢትዮጵያ ያካበተችው ልምድ እና የዲፕሎማሲ ችሎታ በቀጣይ በሚገነቡ ሌሎች ግድቦች ሊገጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን ለማለፍ እገዛ እንደሚያደርግ ዶክተር ያዕቆብ ተናግረዋል፡፡ ዲፕሎማሲያችን በሀገር ደረጃ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ እና የተደራጀ በመኾኑ ወደ ፊትም ይሄ የዲፕሎማሲ ጥንካሬ የበለጠ ከፍ እያለ መሄድ እንዳለበት አመልክተዋል፡፡

እንደ ኢፕድ ዘገባ በቀጣይ በሌሎች ወንዞች ላይ የሚደረጉት ልማቶች በጋራ የውኃ ሀብት የጋራ ተጠቃሚነት መርሕ መቀጠል እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የዓባይ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ባለፈም ለመስኖ፣ ለዓሣ ማጥመድ እና ለመጓጓዣ እንዲሁም ለመዝናኛ ተመራጭ የሚኾን ቦታ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ለአካባቢው የዱር እንስሳት እና ሥነ ምሕዳራዊ ሚዛን ለመጠበቅ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

የዓባይ ግድብ ግንባታ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ነው የተጀመረው፤ ዘንድሮም የግንባታው 13ኛው ዓመት በድምቀት መከበሩ የሚታወስ ነው።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ተሸላሚ!
Next article“የሕዝብን የኢኮኖሚ እና የሰላም ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ታሪካዊ አደራ ተጥሎባችኋል” አቶ ደሳለኝ ጣሰው