የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ተሸላሚ!

42

ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ በዚህ ሳምት የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ተሸላሚ የኾኑበትን ሁኔታ ታሳቢ አድርገን ሥራዎቻቸውን እናስቃኛለን።

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የተወለዱት በሰሜን ሸዋ በምትገኘው አንኮበር 1925 ዓ. ም ነበር፡፡

የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ፣ እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርታቸውን በእንግሊዝ ሀገር በሚገኘው የሥነ ጥበብ አካዳሚ በሥነ ስዕል፣ በቅርፃ ቅርጽ እና በሥነ ሕንፃ ዲዛይን ተከታትለዋል፡፡

በነበራቸው የሥነ ስዕል ዝንባሌ ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩ ሲኾን፤ በወጣትነት ዘመናቸው በ1957 ዓ.ም ከኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ እጅ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ተሸላሚ ለመኾን በቅተዋል፡፡

ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የአራት ዓለም አቀፍ አካዳሚዎች አባል የነበሩ ሲኾኑ በተሰማሩበት የሥነ ሥዕል ጥበብ በዓለም ላይ ከፍተኛ ሚና ለተጫወቱ ታላላቅ ሰዎች የሚሰጠውን “የዓለም ሎሬት” የተሰኘውን ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ ከ97 በላይ የዓለም አቀፍ ሽልማቶችንም ከተለያዩ ተቋማት አግኝተዋል፡፡

በስዕሎቻቸውም ሥርዓተ አምልኮን፣ ማኅበራዊ አኗኗር የማኅበረሰቡን ደስታ እና ሃዘን እና ጀግንነቱን ሥልጣኔውን እና ሀገር ወዳድነትን የሚያንጸባርቁ ሥራዎችን አበርክተዋል፡፡ በተለይም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ካላቸው ጥልቅ ፍቅር እና እምነት በመነጨ ለተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በስቱዲያቸው እና በጸሎት ቤታቸው የሚገኙ መንፈሳዊ ስዕላትን አበርክተዋል፡፡ ከሠሯቸው መካከልም በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ በግድግዳ ላይ የተሠሩ መንፈሳዊ ስዕላትን በቀለም ቅብ፣ በባለቀለም ጠጠሮች፣ በክርክም መስታወቶች እና በሞዛይክ ከታወቁት እና ሥመ ጥር ከኾኑት ሰዓሊ ብላታ እምአዕላፍ ኅሩይ ጋር ሠርተዋል፡፡

በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሙዚየሞች ውስጥም ስዕሎቻቸው በክብር ተቀምጠውላቸው በጎብኚዎች እየታዩ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ ረገድም በስዕሎቻቸው እና በቅርፃ ቅርጾቻቸው አማካይነት ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ሲኾን ‹‹ቪላ አልፋ›› የተሰኘው ባለ 22 ክፍሎች መኖሪያ ቤታቸው እና የግል ስቱዲያቸው ውስጥ ይህንኑ ለማንጸባረቅ ጥረት አድርገዋል፡፡

በቪላ አልፋ ስቱዲዮ ውስጥ የአክሱም ሐውልት፣ የጎንደር ፋሲለደስ፣ የሐረር ግንብ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ ቅዱሳት ስዕላት፣ የተወለዱበት አንኮበር የሚገኘው ቤተ መንግሥት የሚያስደንቁ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ሀገራዊ እሴቶችን አካቶ የያዘ ነው፡፡

እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አፈወርቅ ተክሌ ከሚታወቁባቸው ሥራዎቻቸው ውስጥ፡-

👉 በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ መግቢያ የሚታየው በ150 ካሬ ሜትር ላይ የተሳለው ትልቅ የመስታወት ስዕል፤
👉 በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚገኘውን የመጀመሪያውን የ”ዳግም ቀረበው” ፍርድ ስዕል፤
👉 በሐረር የልዑል ራስ መኮንን ሐውልት፤
👉በአዲግራት የዳግም ምጽዓት ፍርድ ስዕል፤
👉 በለንደን “ታወር ኦፍ ለንደን” የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎት ቤት ከብር እና ከእንጨት የተሠራ የመንበር መስቀል፤
👉 በሩሲያ፣ አሜሪካ እና በሴኔጋል ኤግዚቢሽን ላይ የቀረበው “የመስቀል አበባ” ስዕል፤
👉 “እናት ኢትዮጵያ” የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ምስል እና “ደመራ” ተጠቃሾች ናቸው

—–/////——//////—–/////—–/////——–

ዘመናትን የተሻገረው የተስፋ ቃል!

የሰብዓዊ መብት ታጋዩ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር የዛሬ 56 ዓመት በዚህ ሳምንት ዓለም የሚያስታውስላቸውን ‹‹ወደ ተራራው አናት ወጣሁ›› የሚለውን ንግግራቸውን አሰምተዋል፡፡

ማርቲን ሉተር ኪንግ አፍሪካ አሜሪካውያን ለምርጫም ኾነ ለሁለንተናዊ መብት እና እኩልነታቸው መስዋዕትነት የጠየቁ አታካች ትግሎችን አካሂደዋል፡፡ በቀደመው ዘመን የአፍሪካ አሜሪካውያኑን የመብት ትግል ከመሩ ተሟጋቶች መካከል ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኒየር በአርዓያነት ይጠቀሳሉ፡፡

እኚህ የመብት ታጋይ ከመብት ተሟጋችነታቸው በተጨማሪ በመሳጭ አነቃቂ እና ቀስቃሽ ንግግሮቻቸውም ይታወቃሉ፡፡ አፍሪካ አሜሪካውያን በምድረ አሜሪካ ሁለንተናዊ መብት እና እኩልነታቸው የሚረጋገጥበት ጊዜ እንደሚመጣ በታሰባቸው ጊዜ “ሕልም አለኝ” የሚለውን አስደናቂ ንግግራቸውን አደረጉ፡፡

ኪንግ በሜንፊስ ባደረጉት መሳጭ እና ቀስቃሽ ንግግር ሞታቸው እንደቀረበ ጠቅሰውት ነበር፡፡ እንዳሉትም ተገደሉ፡፡ ኪንግ በዓላማ ተፃራሪዎቻቸው ሴራ ሕይወታቸውን ቢያጡም የመብት ትግላቸው መና አልቀረም፡፡ “ሕልም አለኝ” አሉ፡፡ ሕልማቸው አፍሪካ አሜሪካውያን ባራክ ሁሴን ኦባማን ለዋይት ሐውስ በማብቃት ተምሳሌታዊ ፍቺ አገኘ፡፡

ከቅርብ አስርት ዓመታት ወዲህ በርካታ አፍሪካ አሜሪካዊያን ለታላላቅ መንግሥታዊ ኀላፊነት በቅተዋል፡፡ጄኔራል ኮሊን ፓወል፣ ወይዘሮዎቹ ኮንዶሊዛ ራይስ እና ሱሳን ራይስ እንዲሁም የቅርብ ጊዜዋ ካማላ ሐሪስ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት በመኾን ጭምር ለታላላቅ ኀላፊነት ከበቁ አፍሪካ አሜሪካውያን ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡

የመብት ተሟጋቹ በዘመናቸው የዘር መድልዎ ከነገሠባት አሜሪካ አሻግረው የተስፋይቱ ምድር ሲሉ የጠሯትን እና እኩልነት የነገሰባትን አዲሲቱን አሜሪካ አለሙ፡፡ በአሜሪካ የዘር መድልዎ ችግር ሙሉ በሙሉ ባይወገድም ከማርቲን ሉተር ኪንግ እና ከዚያ ቀደም ከነበሩት ዓመታት ሲነጻጸር በብዙ እጥፍ መሻሻል የሚስተዋልበት ነው፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleጽንፈኛዉ ቡድን ዛሬም በፍኖተሰላም ከተማ ገበያ ላይ በተሰበሰበ ሕዝብ መሀል የሽብር ተግባር ፈጽሟል።
Next articleበግድቡ ኢትዮጵያ ያካበተችው ልምድ እና የዲፕሎማሲ ችሎታ በቀጣይ በሚገነቡ ሌሎች ግድቦች ሊገጥሙ የሚችሉ ፈተናዎችን ለማለፍ እገዛ እንደሚያደርግ የውኃ ፖለቲካ ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ.ር) ተናገሩ፡፡