ጽንፈኛዉ ቡድን ዛሬም በፍኖተሰላም ከተማ ገበያ ላይ በተሰበሰበ ሕዝብ መሀል የሽብር ተግባር ፈጽሟል።

122

ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የክልላችን ሕዝብ በሽብር እየናጠዉ የሚገኘዉ ጽንፈኛ ቡድን ትናንት ሕዝብ በተሰበሰበበት ገበያ መሀል ቦምብ አፈንድቶ በፍኖተሰላም ከተማ ነዋሪዎች እና ከተለያዩ አካባቢዎች ለግብይት በተሰበሰበ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።

በዚህ ጸያፍ የሽብር ድርጊት 34 ሰዎች ሲቆስሉ ከእነዚህ ዉስጥ 11 የሚሆኑት ከባድ ጉዳት አጋጥሟቸዋል። ተጎጅዎች በተለያዩ የህክምና ተቋማት ክትትል እየተደረገላቸዉ ይገኛሉ።

ጽንፈኛ ቡድኑ ራሱ ከያዘዉ እኩይ አላማ ነጻ ሳይወጣ ቁሜለታለሁ ያለውን ሕዝብ መግደል መጀመሩ በግልጽ ግብሩና ዓለማው ምን እንደሆነ የሚያመላክት፤ ለሕዝብ የቆመ ሳይሆን የሌባ፣ የዘራፊና የነፍሰገዳይ ስብስብ መሆኑን ራሱ በድርጊቱ መስክሯል።

የጽንፈኛው ቡድን እብሪት ሕዝብ ሠርቶ እንዳይበላ፣ ነጋዴዉ እንዳይነግድ፣ የግብርና ግብዓት ለአርሶ አደር እንዳይቀርብ እና አርሶ አደሩ ያመረተዉን እንዳይሸጥ ለምን እንቅስቃሴ ተደረገ በሚል በሚፈጽመው እኩይ ተግባር ሕዝባችንን ለማያባራ ፈተና እና ስቃይ ዳርጎታል።

የሽብር ቡድኑ በግምባር የክልሉን እና የመከላከያ ሠራዊታችን ጥምር ምት መቋቋም ሲያቅተው ወርዶ የሽብርና የዘረፋ ተግባር ላይ ተሰማርቷል። ይህ ድርጊቱ ሕዝባችንን በእጅጉ ያሳዘነ እና በታሪክ ተደርጎ የማይታወቅ ጸያፍ ድርጊት ነዉ።

የሕዝብን ጥያቄ ተንተርሶ የግል የፖለቲካ ተልዕኮውን እና ጥቅሙን ለማሳካት እዚህና እዚያ እየረገጠ የሚገኘዉ ጽንፈኛ ቡድን በሠራዉ የሽብር ድርጊት ማኅበራዊ መሰረቴ ከሚለዉ ሕዝብ ተነጥሎ እንደ እብድ ዉሻ ያገኘዉን ሁሉ እየነከሰ ይገኛል።

ይሄን ጽንፈኛ ቡድን በየደረሰበት ሁሉ በመግባት እርምጃ በመዉሰድ የሕዝባችን ሰላም እስኪረጋገጥ የሕግ ማስከበሩ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል በመሆኑ በየደረጃዉ ያለ የጸጥታ መዋቅርና አመራር የድርሻዉን ሊወጣ ይገባል።

ሕዝባችንም የዉስጥ ሰላሙ እስኪረጋገጥ በግምባር ለሚገኘዉ የጸጥታ መዋቅራችን የማያባራ ድጋፉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

በመሆኑም መላ የክልላችን ሕዝብ ይሄን የዉጭ እና የዉስጥ የሽብር ተልዕኮ ይዞ እየፈጸመ እና እያስፈጸመ የሚገኝ ጽንፈኛ ቡድን እንደሕዝብ ሊያወግዘዉ ይገባል።

የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን

መጋቢት 28/2016 ዓ/ም

ባሕርዳር

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዋግ ኽምራን ከሴፍትኔት ተጠቃሚነት ለማላቀቅ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ላይ መሥራት እንደሚገባ የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አማካሪ ተፈራ ካሳ ገለጹ፡፡
Next articleየመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የሥነ ጥበብ ተሸላሚ!