
ባሕር ዳር: መጋቢት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ)“ኢትዮጵያ ታምርት እኛም ሰላሟን እንጠብቅ” በሚል መሪ መልዕክት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ኢንቨስትመንት መምሪያ እና በሰቆጣ ከተማ ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት ከባለድርሻ አካላት ጋር የኢንቨስትመንት ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።
የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪ እና የኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ሹመት ጥላሁን ዋግ ኽምራ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስሱ ወንዞች ባለቤት እንደኾነ ተናግረዋል፡፡ እነዚህን ወንዞች ማልማት ከተቻለ በመስኖ ልማት ዘርፍ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ነው ያስገነዘቡት።
ዋግ ኽምራ በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገ ቢኾንም በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እየዋለ አለመኾኑን ነው አቶ ሹመት ያብራሩት፡፡
ኀላፊው በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ኢንቨስትመንት መምሪያው አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በቀጣይ ለሥራ ማነቆ የኾኑ ችግሮችን በመለየት ኢትዮጵያ እንድታመርት በጋራ ለመሥራት መሰል የኢንቨስትመንት ንቅናቄዎች እንደሚካሄዱ ነው የገለጹት፡፡
በንቅናቄ መድረኩ የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አማካሪ ተፈራ ካሳ አማራ ክልልን በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ውጤት አሳይተዋል ብለዋል።
በክልሉ እየታየ ያለውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት በማስቀጠል ኢንቨስትመቱ ላይ የሚነሱ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ መንግሥት ቁርጠኛ እንደኾነም አስረድተዋል።
ዋግ ኽምራን ከሴፍትኔት ተጠቃሚነት ለማላቀቅ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ያላትን ጸጋ እንድትጠቀም በማድረግ በጋራ መሥራት ይገባልም ነው ያሉት፡፡
በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ያለውን ሰላም በመጠቀም ባለሃብቱ መዋዕለ ንዋዩን እንዲያፈስስ ምቹ መንገዶችን መፍጠር እንደሚገባም አሳስበዋል።
በንቅናቄ መድረኩ የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አማካሪ፣ የአማራ ክልል ቅርስ ቱሪዝም ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ፣ የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የወረዳ አመራሮች፣ ባለሃብቶች እና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!