በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የመንግሥትን የለውጥ ሥራ የሚደግፉ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው፡፡

50

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በመዲናዋ አዲስ አበባ ጨምሮ በሐረሪ ክልል፣በወላይታ ሶዶ እና አርባ ምንጭ ከተሞች በለውጡ መንግሥት የተገኙ ስኬቶችን የሚደግፍ ሕዝባዊ ሰልፎች ናቸው የተካሄዱት፡፡ በመዲናዋ አዲስ አበባ በተካሄደው ሰልፍ ላይ እንደተገለጸው ከተማዋን የብልጽግና ተምሳሌት፣ እንደ ስሟ ውብ፣ ለኑሮ ምቹ እና ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል እንድትኾን የማድረግ ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

በሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ “ሁሌም ድጋፋቸው ላልተለየን የከተማችን ነዋሪዎች አክብሮታችን ከፍ ያለ ነው እናመሠግናለን” ብለዋል። ከንቲባዋ ለውጡ ሀገሪቱን ከፍ ባደረጉ ታላላቅ ሥራዎች እና ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ከፍ ብሎ አንድነት የደመቀበት በአዲስ አበባ ደግሞ የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ተጀምረው የተጠናቀቁበት እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

በሐረሪ ክልል በተካሄደው ሰልፍ ደግሞ ከክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና ሌሎችም ተሳትፈዋል። ሰልፈኞቹ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) መሪነት ባለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት በሰላም ፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር የተገኙትን ስኬቶች አድንቀዋል፡፡ በክልሉም ባለፉት ስድስት ዓመታት በሰላምና ፀጥታ፣ በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት መስኮች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።

በወላይታ ሶዶ እና በጋሞ ዞን በአርባ ምንጭ ከተማ የድጋፍ ሰልፎች የተካሄዱ ሲኾን በሰልፎቹም ባለፉት ስድስት ዓመታት በለውጡ መንግሥት የተመዘገበውን ሁለንተናዊ የልማት ውጤቶች በሕዝቡ ተሳትፎ ማጽናት እንደሚገባ ነው የተገለጸው። ኢዜአ እንደዘገበው የሰልፉ ተሳታፊዎች “ሰላማችን የብልጽግናችን መሠረት በመኾኑ ለሀገራችን ሰላም ተያይዘን እንሠራለን” ብለዋል፡፡ ኅብረ ብሔራዊነትን በማጠናከርም ለሁሉም የተመቸች ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚገባም ነው ሰልፈኞቹ ያስገነዘቡት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የ”ፊቼ ጫምበላላ” በዓል በአብሮነት፣ በሰላም እና በመረዳዳት እሴት የሚከበር በዓል ነው” የሲዳማ ክልል
Next articleዋግ ኽምራን ከሴፍትኔት ተጠቃሚነት ለማላቀቅ በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ላይ መሥራት እንደሚገባ የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን አማካሪ ተፈራ ካሳ ገለጹ፡፡