
ባሕር ዳር: መጋቢት 28/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ዐቢይ ኮሚቴ እስካሁን በተሠሩ ሥራዎች እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱ የድርቅ አደጋውን ለመከላከል የተሠራው ሥራ አበረታች መኾኑ ተመላክቷል፡፡ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በክልሉ የተከሰተውን ድርቅ ጉዳቱን የመቀነስ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የሰው ሕይወት የከፋ ችግር ውስጥ እዳይገባ ድርቁ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡ በክልሉ በ9 ዞኖች፣ በ43 ወረዳዎች፣ በ429 ቀበሌዎች ድርቅ መከሰቱንም አንስተዋል፡፡ በተከሰተው ድርቅ ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ወገኖች ለአደጋ መጋለጣቸውን ነው የተናገሩት፡፡ የክልሉ መንግሥት የተከሰተውን ድርቅ እና ያስከተውልን ችግር መነሻ በማድረግ ምላሽ እየሰጠ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ድርቁ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያስከትል የተናገሩት ኮሚሽነሩ የምግብ አቅርቦት ብቻ ሳይኾን፣ የእንስሳት መኖ፣ ውኃ፣ መድኃኒት እና ሌሎች ድጋፎች እንደሚያስፈልጉ ነው ያነሱት፡፡
በውይይቱ ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር እንደሚገባም አቅጣጫ መቀመጡንም አመላክተዋል፡፡ እስካሁን የተሠራው ሥራ አበረታች እና ችግሩን መቀነስ የቻለ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ መጪውን ጊዜ ታሳቢ በማድረግ በማኅበረሰቡ ዘንድ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ በቅንጅት ይሠራልም ብለዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ችግሩን ታሳቢ በማድረግ በጀት መድቦ ለወገኖች ድጋፍ የሚኾን ግዥ መፈፀሙንም ተናግረዋል፡፡ ከተመደበው 410 ሚሊዮን ብር በ300 ሚሊዮን ብር ግዥ መፈጸሙንም አስታውቀዋል፡፡ አሁንም ተጨማሪ መጠባበቂያ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡
በክልሉ ያለው የተረጂ ቁጥር እና የፌዴራል አደጋ ስጋት የሰጠው ምላሽ የመጣጣም ጉድለት እንደለበትም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ በድርቅ የተጎዱትን እና ተፈናቃዮችን ጨምሮ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ወገኖች ድጋፍ እንደሚሹ አመላክተዋል፡፡ በክልሉ 3 ነጥብ 9 ሚሊዮን እርዳታ የሚፈልጉ ወገኖ መኖራቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሩ ለሁሉም ምላሽ መስጠት ይከብዳል፤ ነገር ግን 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ወገኖች ምላሽ ያስፈልጋቸዋል ነው ያሉት፡፡ የክልሉ መንግሥት እና የፌደራል መንግሥት እያደረጉት ያለውን ድጋፍ እናደንቃለን፣ ነገር ግን ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ረጂ ድርጅቶችም ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውን የተናገሩት ኮሚሽነሩ አሁን ካለው ችግር አንጻር ተጨማሪ ድጋፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ አምርተው ራሳቸውን እስኪችሉ ድረስ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡ የሰውን ሕይወት ማቆየት የሚያስችል ሥራ ተሰርቷል፤ ነገር ግን የተጠናከረ ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ እንስሳትን ታሳቢ ያደረገ ድጋፍ እየተደረገ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን በክልሉ የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል እና ለመቀነስ የተሠሩ ሥራዎች ድርቁ ሊያስከትለው የሚችለውን ጉዳት የቀነሱ ናቸው ብለዋል፡፡ “ለአደጋ መከላከል እና ጉዳቱን መቀነስ የተሰጠው ምላሽ ፈጣን ነበር” ነው ያሉት፡፡ የተሰጠው ምላሽ አሁንም መቀጠሉን ነው የተናገሩት፡፡
ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ የክልሉ መንግሥት በልዩ ትኩረት መሥራቱንም አስታውቀዋል፡፡ እስካሁን በተሠራው ሥራ ጉዳቱን መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት፡፡ የችግሩን ስፋት በመለየት ምላሽ የመሥጠት ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል፡፡ የሰዎችን ብቻ ሳይኾን የእንስሳትን ጉዳት በመለየት ጥሩ የሚባል ድጋፍ መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡ ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት የጋራ እቅድ ይዞ ለመሥራት ጥረት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ በቅንጅት መሥራት ሲቻል ችግሮችን መፍታት ይቻላል ብለዋል፡፡
የእንስሳት መድኃኒት አቅርቦት ላይ ጥሩ ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል፡፡ ትክክለኛውን ጉዳት ታሳቢ በማድረግ ለእንስሳት መኖ ማቅረብ ይገባልም ብለዋል፡፡ በሰዎች የመድኃኒት አቅርቦት ላይ ያለው ክፍተት መስተካከል እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡ እየተሰጠ ያለው ድጋፍ ችግሩን የሚያስታግስ እና የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ያደረገ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
በቀጣይ ሥራዎችን ማስፋት ይገባል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ዘር እና የአፈር መዳበሪያ በማቅረብ ከችግር የሚወጡበትን መንገድ ማመቻቸት ይጠበቅበናል ብለዋል፡፡ ለአቅርቦት እንቅፋት የኾነውን የሰላም እና የጸጥታ ችግሩን መፍታት እንደሚጠበቅም አመላክተዋል፡፡ አሁን ላይ በሰዎች እና በእንስሳት ላይ ሞት የሚያደርስ የድርቅ ችግር አለ ተብሎ አይወሰድም ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ነገር ግን ችግሩ ተለዋዋጭ በመኾኑ የሚመጡትን ችግሮች ለመቋቋም የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን መሥራት ይጠበቃል ብለዋል፡፡ ዝናብ ሲጥል ሊመጣ የሚችለውን የጤና ችግር እና የጎርፍ አደጋ ታሰቢ ያደረገ ሥራ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የድርቅ አደጋ ያስከተለው ችግር በትክክል እንዲገለጽ እና ፈጣን ምላሽ እንዲሰጠው ይፈለጋል ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ ምፍትሔ እና አንድነትን ሊያመጡ የሚችሉ አካሄዶችን መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ለተጎጂ ወገኖች ድጋፍ በተገቢው መንገድ እንዲደርስ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ ተፈናቃዮችን ታሳቢ ያደረገ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል፡፡ የተጎዱ ወገኖችን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረግ ከሰብዓዊነት መውረድ መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡ ተፈናቃዮችን መነገጃ ማድረግ እንደማይገባም አሳስበዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!