
ባሕር ዳር: መጋቢት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ተስፋየ አስማረ በዘንድሮው የመኸር እርሻ 250 ሺህ ሄክታር መሬት በሰብል ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት፡፡ በምርት ዘመኑ 11 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘትም ግብ ተቀምጦ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ይህን ግብ ለማሳካትም 894 ሺህ 120 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሞ የማጓጓዝ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ ግዥ ከተፈፀመው ማዳበሪያ ውስጥ እስካሁን 572 ሺህ 625 ኩንታል ወደ ዩኒየኖች መጋዝን መግባቱን ገልጸዋል፡፡ መምሪያ ኀላፊው ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራትም 111 ሺህ 655 ኩንታል ማዳበሪያ ተጓጉዟል ነው ያሉት።
57 ሺህ 902 ኩንታል የሚኾነው በኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል ነው የተባለው። ስርጭቱም ከአቅርቦቱ ጋር ሲነጻጸር ውስንነት ያለበት በመኾኑ አመራሩ እና ባለሙያው ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ አሳስቧል፡፡ አርሶ አደሩ ማዳበሪያውን በእጁ በማስገባት ለዘር ወቅት ቅድመ ዝግጅቱን እንዲጨርስ መምሪያ ኀላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!