አልማ በደብረ ብርሃን ከተማ በ10 ትምህርት ቤቶች ለቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ምገባ እንደሚያስጀምር ገለጸ።

26

ደብረ ብርሃን: መጋቢት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ልማት ማኅበር (አልማ) በደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር ውስጥ በሚገኙ 10 ትምህርት ቤቶች ለቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ምግባ እንደሚያስጀምር ገልጿል። ለዚሁ ተግባር የሚስፈልጉ ቁሳቁሶችን በየትምህርት ቤቶች እያሰራጨ መኾኑንም ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ ጠቁሟል።

በትምህርት ቤቶቹ 1ሺህ 344 የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ እንደሚኾኑም የሰሜን ሸዋ ዞን አልማ ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቶ ደረጀ ፍቅሬ ገልጸዋል። ድጋፉን ለማድረግ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች የበጀት ምንጭ መኾናቸውንም አቶ ደረጀ ጠቁመዋል። ቁሳቁሶቹን የከተማው የተማሪዎች የምገባ አሥተባባሪ ኮሚቴው ተገኝቶ ተመልክቷል። አስተያየት ሲሰጡም አልማ ሰው ተኮር ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በአልማ አሥተባባሪነት ወጭ ተደርጎ የአዋቂ እና የሕጻናት የፕላስቲክ መንበር እና ጠረንጴዛዎች፣ ምንጣፎች እና ሌሎችም የተግባር ተኮር ትምህርት መስጫ ቁሳቁሶች ተዘጋጅተዋል። ለሕጻናትን በተግባር የተደገፈ ትምህርት መሰጠቱ ለመደበኛ ትምህርታቸው አቅም እንደሚኾናቸውም ተጠቁሟል።

እንደከተማ ለ25 ሺህ ተማሪዎች በ47 የመደበኛ እና ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ምገባ ለማስጀመር በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ከደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የእንሰሳትን ሞት ለማስቀረት ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ፡፡
Next articleከ572 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አካባቢው መግባቱን የምዕራብ ጎጃም ዞን ገለጸ፡፡