በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የእንሰሳትን ሞት ለማስቀረት ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ፡፡

24

ባሕር ዳር: መጋቢት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በተፈጠረው የዝናብ እጥረት በአንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ ተከስቷል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የተከዜ ተፋሰስ አካባቢ አንዱ ነው፡፡ በተለይም በዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና በሰሜን ጎንደር ዞን ድርቁ የከፋ ነው፡፡ በተከሰተው ድርቅ ዜጎች እጃቸውን ለእርዳታ ዘርግተዋል፡፡ እንስሳትም ተጎድተዋል፡፡

የዋግኸምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማሥተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ምኅረት መላኩ በተፈጠረው ድርቅ እንስሳት መሞታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተደረገው ድጋፍ የእንስሳትን ሞት መቀነስ ቢቻልም አሁንም የእንስሳት ሞት መኖሩን ነው የተናገሩት፡፡ የአንስሳትን ሞት ለመቀነስ ወደ ሌሎች ወረዳዎች የመውሰድ እና በተቻለ መጠን መኖ የማድረስ ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል፡፡ በተከዜ ዳር የመስኖ ልማትም እንስሳትን የመኖ ተጠቃሚ የማድረግ ተግባር መፈጸሙንም ተናግረዋል፡፡

የተሻሉ ወረዳዎችም በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የመኖ ድጋፍ እንዲያደርጉ መሠራቱንም አንስተዋል፡፡ ድርቁ እንስሳት ላይ ከፍተኛ አደጋ የደቀነ መኾኑንም ነው የተናገሩት፡፡ የክልሉ የእንስሳት ሃብት በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡ የእንስሳት ሞትን ለማስቆም ከፍተኛ ርብርብም እንደሚጠይቅ ነው ያስገነዘቡት፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሰላምይሁን ሙላት በዞኑ በተፈጠረው ድርቅ እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡ የእንስሳት መኖ ድጋፍ እንደሚስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ውኃ፣ መኖ እና የእንስሳት ክትባት እንደሚያስፈልግም ነው የተናገሩት፡፡
የእንስሳት መኖ ለማቅረብ ሰፊ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡ ድርቁ ውኃ በማድረቁ ለእንስሳት ውኃ ለማቅረብ አስቸጋሪ ኾኖ መቆየቱንም አንስተዋል፡፡ የእንስሳትን ሞት ለማስቀረት ሰፊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል እንስሳት እና ዓሳ ሃብት ልማት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ዳዊት ገዳሙ ክልሉ ሰፊ የእንስሳት ሃብት ክምችት ያለበት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ያለውን እንሰሳት በተገቢው አልምቶ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡ የእንሰሳት መኖ ልማት ቅድሚያ ተሰጥቶ የሚሠራበት መኾኑንም አመላክተዋል፡፡

የመኖ ልማትን ከፍ በማድረግ የእንስሳት ተዋጽኦ እንዲያድግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ በተሠሩ ሥራዎች አበረታች ውጤቶች እየተገኙ ነው ያሉት ኀላፊው የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡ ዝርያ ማሻሻል ሌላኛው በትኩረት የሚሠራበት ጉዳይ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡ መከላከልን መሠረት ያደረገ የእንስሳት ጤና አጠባበቅ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ በወረዳዎች እና በቀበሌዎች የእንስሳት ጤና ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት እየሠጡ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡

ድርቅ በሚከሰትበት ጊዜ በባለሙያ የታገዘ የችግሩን ስፋት በማየት የመፍትሔ አቅጣጫ የማስቀመጥ ሥራ እንደሚሠራ ነው የተናገሩት፡፡ ዘንድሮ በተከሰተው ድርቅም ጥናት ለማድረግ ጥረት መደረጉን ነው የገለጹት፡፡ የጸጥታው ችግር ግን ለሥራቸው ፈተና እንደኾነባቸው ተናግረዋል፡፡ በድርቅ የተጎዱ እንስሳትን ከአደጋ ለመታደግ እቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል፡፡ የመጀመሪያው የሚመከረው የእንሰሳት ባለቤቶችን በማሳመን ቁጥራቸውን እንዲቀንሱ የማድረግ ነው ብለዋል፡፡

የባለሙያዎችን ምክረ ሃሳብ መሠረት በማድረግ የእንስሳት ቁጥርን መቀነስ የመጀመሪያው አማራጭ መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ የተሻለ መኖ ወደሌለባቸው አካባቢዎች ማስጠጋት እና መኖ ባለባቸው አካባቢዎች መኖ በድጋፍ እንዲያሠባሥቡ ማድረግ ሌሎች አማራጮች ናቸው ብለዋል፡፡

ከዚህ ያለፈ ሲኾን መንግሥት አጋር አካላትን በማስተባበር መኖዎችን በድጋፍ እንዲያቀርብ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡ አብዛኛዎቹ ሥራዎች የሚሠሩት በዚያው አካባቢ ባለው መዋቅር መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትናም ለሰዎች ብቻ ሳይኾን ለእንስሳትም ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ብለዋል፡፡ የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም ችግሮች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡

በተደረገው ጥናት መሠረት የወጣውን እቅድ ለማስፈጸም እየሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የቁም እንሰሳት ግብይትን በማሻሻል በሺዎች የሚቆጠሩ የቁም እንሰሳት እንዲሸጡ መደረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡

243 ቶን የሚኾን መኖ ከዩኒቨርሲዎች እና ከተለያዩ ፕሮጄክቶች በማሠባሠብ ድርቅ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች ለማሰራጨት ጥረት መደረጉን ነው የገለጹት፡፡ የተሠራው ሥራ ግን አሁንም በቂ አለመኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ መኖ የማልማት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራበት የሚገባ ነውም ብለዋል፡፡

ወንዞች እና እርጥበት ባሉባቸው አካባቢዎች የእንስሳት መኖ እንዲለማ ማድረግ አስፈላጊ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የመኖ ልማት አስፈላጊ በመኾኑ ዘር የማሰራጨት ሥራ ተሠርቷል ተብሏል፡፡ የእንስሳት መኖ ልማት ሥራ መሠራቱንም ገልጸዋል፡፡ የተሻለ መኖ ካለባቸው አካባቢዎች የተሠበሠበው መኖ በትራንስፖርት ችግር ምክንያት አለመጓዙንም አስታውቀዋል፡፡

የእንሰሳት የህክምና ቁሳቁስ ለማቅረብ ጥረት መደረጉንም አንስተዋል፡፡ የጸጥታ ችግሩ መድኃኒቶችን ለማቅረብ አስቸጋሪ መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡ የጸጥታ ችግሩ በሚፈለገው ልክ እያሠራ አለመኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበቀሪዎቹ የበልግ ወራት ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
Next articleአልማ በደብረ ብርሃን ከተማ በ10 ትምህርት ቤቶች ለቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ምገባ እንደሚያስጀምር ገለጸ።