በቀሪዎቹ የበልግ ወራት ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

35

አዲስ አበባ: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የነበረውን የወቅት አጋማሽ የአየር ጠባይ ግምገማ እና በሚቀጥሉት የበልግ ወራቶች የሚጠበቀውን የአየር ጠባይ አስመልክቶ ገለጻ ተደርጓል፡፡ ባለፉት ሁለት የበልግ ወራት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በኾኑት በደቡብ፣ በደቡብ ምስራቅ እና በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ የኾነ የዝናብ መጠን እና ስርጭት እንደነበራቸው ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

በተሰጠው ትንበያ መሠረት የወቅቱ የዝናብ አጀማመር በተለይም በሰሜን ምሥራቅ፣ መካከለኛው እና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ላይ ቀድሞ እንደጀመረ ተናግረዋል፡፡ ይህም የኾነበት ምክንያት በትሮፒካል ፓስፊክ ውቅያኖስ የባሕር ወለል ሙቀት ከመደበኛ በላይ መሞቅ እንዲሁም የሰሜናዊ ሕንድ ውቅያኖስ መደበኛ የባሕር ወለል ሙቀት መጠን አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደነበረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጅ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈጠነ ተሾመ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ወራት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ የተስተዋለ መኾኑን አቶ ፈጠነ ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም 40 በሚደርሱ የሀገራችን አካባቢዎች ላይ በ24 ሠዓት ውስጥ ከ30 እስከ 96 ሚሊ ሜትር ዝናብ መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡ በልግ ዋነኛ እና ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በኾኑት የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከደመበኛ በላይ የዝናብ መጠን እና ስርጭት እንደነበረም ተገልጿል፡፡

ይህም ሁኔታ የበልግ የግብርና ሥራን ለማከናዎን እንዲሁም የተለያዩ ተፋሰሶች የውኃ መጠን እንዲሻሻል እና ለአርብቶ አደሮች እና ከፊል አርብቶ አደሮች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደነበረው ሰፋ ያለ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ በቀሪዎቹ የበልግ ወራትም የትሮፒካል ፓስፊክ ውቅያኖስ የባሕር ወለል ሙቀት ከመደበኛ በላይ መሞቅ እንዲሁም የሰሜናዊ ሕንድ ውቅያኖስ መደበኛ የባሕር ወለል ሙቀት መጠን ኾኖ ሊቆይ እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ ሲሉ አቶ ፈጠነ ጠቅሰዋል፡፡

በሚያዚያ እና በግንቦት ወራትም የበልግ ዝናብ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ላይ በተሻለ ጥንካሬ እንደሚቀጥል ተነግሯል፡፡ በልግ ዋነኛ የዝናብ ወቅታቸው በኾኑት የደቡብ እና ደቡብ ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖራቸዉ የምዕራብ አጋማሽ መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ፤ የሰሜን ምሥራቅ፣ የመካከለኛው እና የምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ የኾነ ዝናብ ሊያገኙ እንደሚችሉ በትንበያው ተመላክቷል ብለዋል።

ኅብረተሰቡ በቀሪ የበልግ ወራቶች የሚጠበቀውን የአየር ጠባይ ትንበያን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት እና የሚገኘውን ከመደበኛ በላይ የኾነ የዝናብ መጠን እና ስርጭት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ በዚህ ወቅት የሚካሄደውን የግብርና እንቅስቃሴ እና ሌሎች ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሥራዎችን ከባለሙያዎች ጋር በመመካከር ማከናወን ያስፈልጋል ብለዋል።

አልፎ አልፎ ከሚኖር ተደጋጋሚ ከባድ ዝናብ ጋር በተያያዘ ለጎርፍ ተጋላጭ በኾኑ ረባዳማ ቦታዎች፣ ወንዝ ዳር እና ከተሞች አካባቢ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሥራዎች ላይ ተጽዕኖ ሊያደርስ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ሊያደርስ የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ የሚያስችሉ የጥንቃቄ ሥራዎችን ከወዲሁ ማከናዎን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተያያዘም የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አዲስ የሚያስገነባውን የቢሮ ግንባታ አስጎብኝቷል። ግንባታው በቀጣይ 3 ወራት ተጠናቶ በዘመናዊ እና በአዲስ መልክ ሥራ ይጀምራል ተብሏል፡፡

ዘጋቢ፦ ራሄል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleዘራፊው ቡድን በደጀን ወረዳ የአካባቢውን ወጣት በሀሰት ፕሮፖጋንዳ እያሳመነ ሲያሰለጥንበት የነበረውን ማሠልጠኛ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ፡፡
Next articleበድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የእንሰሳትን ሞት ለማስቀረት ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ፡፡