ዘራፊው ቡድን በደጀን ወረዳ የአካባቢውን ወጣት በሀሰት ፕሮፖጋንዳ እያሳመነ ሲያሰለጥንበት የነበረውን ማሠልጠኛ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ፡፡

73

ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ ዝብልብሊት ቀበሌ ላይ የክፍለ ጦሩ ቃኝ የኮር መሃንዲስ እና የወረዳው ፀጥታ ኀይል በጥምረት በጠላት ላይ የማያዳግም እርምጃ ወስደዋል። ዘራፊው ቡድን የአካባቢውን ወጣት በሀሰት ፕሮፖጋንዳ እያሳመነ ሲያሰለጥንበት የነበረውን ማሠልጠኛ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ ማድረግ መቻሉንም የክፍለ ጦሩ አዛዥ ኮሎኔል አይቼው ግለጠው ገልጸዋል፡፡

የፀጥታ ኀይሉ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ባገኘው መረጃ መሠረት ወደ ስፍራው በመንቀሳቀሱ በርካታ የጽንፈኛው ኀይል መሳሪያውን ጥሎ ለመፈርጠጥ ተገድዷል ብለዋል። በአካባቢው የተረጋጋ ሰላምን ለማስፈን ተልዕኮ አንግቦ የተጓዘው ሠራዊት በማሠልጠኛው ላይ በወሰደው እርምጃ ሰባት ሲመቱ ሁለት የጽንፈኛው ኀይል አሠልጣኝ ዘጠኝ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ እና ትጥቅ መማረክ መቻሉንም ኮሎኔል አይቼው ገልጸዋል።

የመከላከያ ሠራዊት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረው በጉብያ ንዑስ ወረዳ ገተማና ውላት ቀበሌዎች 12 የጽንፈኛው አባላት ሲመቱ ሦሰት ከነ ትጥቃቸው መማረካቸውን መቶ አለቃ ይማም በዛ ተናግረዋል፡፡ በየጁቤ ወረዳ ግዳጅ ላይ የሚገኘው ሬጅመንት ከክልሉ ፀጥታ ኀይል ጋር ተቀናጅተው ጽንፈኛው ሲጠቀምበት የነበረ አምስት ሞተር ሳይክል በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን መቶ አለቃ ሸሪፍ ሙሳ ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዲያስፖራው በሀገር ውስጥ ልማት ተሳታፊ እንዲኾኑ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል” አቶ ዳንኤል ደሳለኝ
Next articleበቀሪዎቹ የበልግ ወራት ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡