
ባሕር ዳር: መጋቢት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ከአማራ ክልል የርእሰ መሥተዳድሩ የዲያስፖራ ጉዳዮች አማካሪ ጋር በባሕር ዳር ከተማ ውይይት አካሂዷል። ውይይቱ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ትውልድ ኢትዮጵያዊያንን በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች እና በመኖሪያ ቤት ልማት ተሳታፊ ለማድረግ ያለመ ነው።
በኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት የተዘጋጁ እና በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በሀገር ውስጥ የልማት አማራጮች ተሳታፊ የሚያደርጉ መነሻ ፓኬጆች ለውይይት ተሳታፊዎች ቀርበው ሃሳብ እና አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል። የርእሰ መሥተዳድሩ የኢኮኖሚ ጉዳይ አማካሪ ቀለመወርቅ ምሕረቴ ዲያስፖራው በሀገር ውስጥ የልማት ተሳታፊ እንዲኾን ፓኬጅ ተዘጋጅቶ ውይይት መደረጉ መልካም ጅምር መኾኑን አንስተዋል።
በውጭ የሚኖሩ ትውልድ ኢትዮጵያዊያንን በአግባቡ ባለመጠቀማችን ምክንያት በርካታ እድሎች እንዳለፉ አንስተዋል፡፡ አቶ ቀለመወርቅ በሀገር ውስጥ የማልማት አቅም ያላቸውን ዲያስፖራዎች በመለየት ችግሮቻቸውን መፍታት እና መግባባት ይጠበቅብናል ብለዋል። የአሠራር ማነቆዎችን መፍታት፣ የተንዛዛውን አሠራር ማሻሻል እና ቀልጣፋ ሥርዓት መገንባት ተገቢ ነውም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት የዲያስፖራ ማኅበረሰብ ልማት ተሳትፎ ዳይሬክተር ነብዩ ሰለሞን የፓኬጆቹ ዋና ዓላማ ዲያስፖራውን በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ተሳታፊ እንዲኾን ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል። ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሀገር ውስጥ የልማት አማራጮች ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲኾኑ ከማድረጉ በተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ አቅማችንን ማሳደግ የሚያስችል መኾኑንም ገልጸዋል።
ዲያስፖራው የቤት ባለቤት እንዲኾን መሥራት በሀገሩ የሰላም እና የልማት ጉዳይ ባለቤት እንዲኾን ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት አቶ ነብዩ፡፡ በአማራ ክልል የርእሰ መሥተዳድሩ ዲያስፖራ ጉዳዮች አማካሪ አላዩ መኮንን በበኩላቸው በክልሉ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በክልሉ የነበረው የዲያስፖራው ተሳትፎ መቀነሱን ገልጸዋል።
ዲያስፖራው ያለበትን ችግር መለየት፣ አቅርቦ ማወያየት እና የማልማት አቅማቸውን በመረጃ ላይ ተመስርቶ የማጥራት ሥራ ይሠራል ብለዋል። በኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት በኩል የተዘጋጀው መነሻ ፓኬጅ ወደ ተግባር ሲገባ ራሱን የቻለ የአሠራር መሥፈርት እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ አቶ አላዩ የተቀዛቀዘውን የዲያስፖራ ተሳትፎ ለማነቃቃት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸውም አንስተዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዳንኤል ደሳለኝ በሰጡት ማጠቃለያ በገፊና ሳቢ ምክንያቶች ከሀገራቸው የወጡ “ዲያስፖራዎች በሀገር ውስጥ የልማቱ ተሳታፊ እንዲኾኑ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል” ብለዋል። በርካታ ሀገራት ለውጥ ያመጡት በዲያስፖራዎቻቸው የተቀናጀ ተሳትፎ ነው ያሉት ኀላፊው የክልላችን ዲያስፖራዎች ለአካባቢያቸው ልማት አቅም አንዲኾኑ ማድረግ እንደሚገባም ገልጸዋል።
በሀገራችን የልማት ጉዳይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸውን ወገኖች ማወያየት፣ የማልማት ፍላጎታቸው መለየት፣ በአሠራር በኩል የሚስተዋሉ ማነቆዎችን በመፈተሽ ኢንቨስት የማድረግ አቅም ላላቸው ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!