ሕዝቡ ጦርነት በቃን ብሎ ወደ ልማት በመመለስ ለሰላም ዋጋ መክፈል እንዳለበት የሰሜን ጎንደር ዞን ገለጸ፡፡

28

ደባርቅ: መጋቢት 27/2016 ዓ.ም (አማኮ) የባሕር ዳር – ጎንደር ኮማንድ ፖስት በሰሜን ጎንደር ዞን ከዳባት እና ደባርቅ ወረዳ ከተማ ነዋሪዎች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከእናቶች እንዲሁም ወጣቶች ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሕዝባዊ ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የሰሜን ምዕራብ ዕዝ አዛዥ እና የባሕርዳር-ጎንደር ኮማንድ ፖስት ሠብሣቢ ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ እንደተናገሩት በጽንፈኛ ኀይሉ ላይ እየተወሰደ ባለው የማያዳግም እርምጃ አሁናዊ የአማራ ክልል የፀጥታ ሁኔታ እየተሻሻለ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር በተደረጉ ሰፉፊ ውይይቶች እና የየአካባቢዎቹን መዋቅር በማጠናከር እና የፀጥታ ኃይሉን አቅም በመገንባት የተሻለ ሰላም ማምጣት እንደተቻለም አስረድተዋል።

የሰላም ጥያቄ የሚመለሰው በሰላም እንጂ በጦርነት እንዳልኾነም ሌተናል ጄኔራል ብርሃኑ በቀለ ጠቁመዋል፡፡ መንግሥት ከየትኛውም የታጠቀ ኃይል ጋር ለውይይት በሩ ክፍት መኾኑንም አስረድተዋል፡፡ ከውይይት ውጪ ፍላጎታቸውን በኀይል ለማሳካት የሚፍጨረጨሩ ጽንፍ የወጡ ኀይሎች የተሳሳተ መንገድ እየተከተሉ መኾኑን ሊገነዘቡ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ወደ ሥልጣን የመምጫውን መንገድ በጉልበት የማድረግ ልምድ መቅረት አለበትም ነው ያሉት፡፡ አባቶች ደም እና አጥንታቸውን ከስክሰው ያቆዩአትን ሀገር ማንም ሊያፈርሳት ሲነሳ ከዳር ኾኖ መመልከት ተገቢ አለመኾኑን በመግለጽ ሁሉም የበኩሉን ኀላፊነት እንዲወጣ ጠይቀዋል። የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዲያቆን ሸጋው ውቤ የሰላምን ዋጋ ሕዝቡ በሚገባ ያውቀዋል ነው ያሉት፡፡ ሕዝቡ ጦርነት በቃን ብሎ ወደ ልማት ከመመለስም ባሻገር ለሰላም ዋጋ መክፈል እንዳለበት አሳስበዋል።

የሰሜን ኮንደር ዞን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረው ነዋሪዎቹ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የኑሮ ውድነት እና አለመረጋጋት እንደተፈጠረባቸው አስረድተዋል፡፡ ለሰላም ከፀጥታ ኀይሉ ጎን እንደሚኾኑም ነው የተናገሩት፡፡ መንግሥትም ያኮረፉትን አቅርቦ በማነጋገር የሚፈጠሩ ቅሬታዎችን መፍታት ይኖርበታል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከ800 በላይ በሚኾኑ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ ሥራ ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።
Next article“የዲጂታል የፋይናንስ ሥርዓት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከፍተኛ ዕድገት እያስመዘገበ ነው” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ