ከ800 በላይ በሚኾኑ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ ሥራ ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።

16

አዲስ አበባ: መጋቢት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ተግባራት ዙሪያ ለመገናኛ ብዙኀን ማብራሪያ ሰጥቷል። ማብራሪያውን የሰጡት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ 1ሺህ 300 የሚኾኑ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች ለልየታ የተመረጡ ሲኾን ከእነዚህ ዉስጥ ወደ 800 በሚኾኑት ልየታው መጠናቀቁም ገልጸዋል።

በአፋር፣ በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በሀረሪ ክልል እና በሁለቱ ከተማ አሥተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ መጠናቀቁንም ቃል አቀባዩ ጠቅሰዋል። በሱማሌ እና በኦሮምያ ክልል የተሳታፊዎች ልየታ እየተጠናቀቀ መኾኑን የገለጹት ቃል አቀባዩ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የልየታ ሥራዎች አልተጀመሩም ብለዋል።

በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ልየታ ለማካሄድ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መሠራታቸውን የገለጹት ቃል አቀባዩ በአማራ ክልል ለልየታው የሚያግዙ ተባባሪ አካላት ተለይተዋል። በቀጣይ ተባባሪ አካላትን በማሠልጠን ወደ ልየታ ሥራ ይገባልም ብለዋል። ምክክሩን አሳታፊ እና አካታች ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል። በልየታው የተለዩ ተሳታፊዎች ከወከላቸው ማኅበረሰብ ጋር በመወያየት የአጀንዳ ግብዓት በተገቢዉ መንገድ እንዲያዘጋጁ ጥሪ ቀርቧል።

ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የ150 ብር መድኃኒት በአንድ ሺህ ብር”
Next articleሕዝቡ ጦርነት በቃን ብሎ ወደ ልማት በመመለስ ለሰላም ዋጋ መክፈል እንዳለበት የሰሜን ጎንደር ዞን ገለጸ፡፡