“የ150 ብር መድኃኒት በአንድ ሺህ ብር”

121

ባሕር ዳር: መጋቢት 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም በታጣ ጊዜ ሕሙማን የሚታከሙባቸው የጤና ተቋማት ይዘጋሉ፤ ቢከፈቱም በውስጣቸው መድኃኒት የለም፤ ሐኪሞች ታካሚዎቻቸውን በተገቢው መንገድ እንዳያገለግሉ የቁሳቁስ እጥረት ያጋጥማቸዋል፤ ታካሚዎች በመድኃኒት እጥረት ምክንያት ለሕመም ይዳረጋሉ፤ አለፍ ሲልም በመድኃኒት እጥረት ላይመለሱ ያልፋሉ፡፡

የሰላም እጦት ሕጻናትን ያለ አሳዳጊ፣ አዛውንቱን ያለ ጧሪና ቀባሪ ያስቀራል፡፡ የሀገሬው ሰው መሽቶ በጠባ ቁጥር በሰላምታው ሁሉ “ሰላም ጤና ይስጥልኝ” እያለ ሰላምና ጤናን አብዝቶ እና አጣምሮ ይመኛል፡፡ ጤናን ለመጠበቅ ሰላም መኾን ያስፈልጋልና፡፡ በአማራ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የጤና ሥርዓቱ ተጎድቷል፡፡ ወላድ እናቶች በነጻነት አይከታተሉም፣ ምጣቸው በመጣ ጊዜም በነጻነት ሄደው በባለሙያ አይገላገሉም፤ ለእናቶች ጤና የሚተጉ አምቡላንሶች እንደወትሮው በነጻነት አይንቀሳቀሱም፤ ይልቅስ በመንገድ እየተያዙ ይወሰዳሉ፣ የሕሙማን ማመላሻ ሳይኾን የታጣቂዎች ንብረት ይኾናሉ፡፡ ሕሙማን በችግር ውስጥም ኾነው ወደ ጤና ተቋም ሲሄዱ መድኃኒት ያጣሉ፡፡ እንድናለን የሚል ተስፋ ሰንቀው ቢሄዱም ያለመፍትሔ ይመለሳሉ፡፡

ነዋሪነታቸው በምዕራብ ጎጃም ዞን ነው፡፡ ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸውን ትተነዋል፡፡ እናታቸው የልብ ሕመም አለባቸው፡፡ በእድሜ የገፉ እናታቸውን ለሰባት ዓመታት ለዘለቀው ጊዜ በወር አንድ ጊዜ ወደ ጤና ተቋም ይወስዳሉ፡፡ የታዘዛላቸውን መድኃኒትም እየያዙ ወደ ቀያቸው ይመለሳሉ፡፡ የሰላም እጦት ከተፈጠረ ወዲህ ግን አስቸጋሪ ኾኖባቸዋል፡፡ ለወትሮው ጤናቸውን አግኝተው የሚያርፉበትን ይመኙ ነበር እንጂ መድኃኒት አጣለሁ፣ መንገዶች እየተዘጉ በስጋት እቀራለሁ ብለው አስበው አያውቁም ነበር፡፡

“በእድሜ የገፋች እናት አለችኝ፣ ለሰባት ዓመታት እየተመላለሰች የታከመች፡፡ ግጭት ከተፈጠረ ወዲህ እንደተለመደው ወደ ሐኪም ቤት ይዤያት ስመጣ መድኃኒት የለም እባላለሁ፡፡ የመድኃኒት እጥረት አለ ይሉኛል፡፡ መስመር ላይ ችግር ስላለ መድኃኒት እንደተፈለገ አይገባም ነው የሚባለው፤ ሲያገኙ ይሰጡናል” ነው የሚሉት አስታማሚዋ፡፡

እኒህ አስታማሚ ለሰባት ዓመታት እናታቸውን ሲያሳክሙ እንደዚህ ወቅት የፈተናቸው ጊዜ እንዳልነበር ያስታውሳሉ፡፡ እናታቸው ከሚወስዱት ሦስት የመድኃኒት ዓይነት ሁሉም በመንግሥት ጤና ተቋም ባይገኝም ለመግዛት አይቸገሩም ነበር፡፡ አሁን ግን ይሄን ማድግ ከባድ ኾኗል፡፡ “እስከዛሬ መድኃኒት በየወሩ ነበር የምወስደው፡፡ ሰሞኑን ግን ሳነጋግራቸው መድኃኒት የለም አሉኝ፡፡ መድኃኒት የለም ስባል ከግል ሄጄ አንድ ሺህ ብር ገዛሁ፡፡ ከግል አንድ ሺህ ብር የገዛሁት መድኃኒት ከመንግሥት መቶ ሐምሳ ብር ነው፡፡ በአንድ ሺህ ብር እና በመቶ ሐምሳ ብር መካካል ከፍተኛ ልዩነት አለ፡፡ ተቸግረን ስንሄድ የምንፈልገውን አናገኝም፡፡ የመስመር ችግር ስላለ፣ መድኃኒት አይመጣም እንባላለን፤ ግማሹን እንኳን ባገኘሁ” ይላሉ አስታማሚዋ፡፡

አስታማሚዋ ከማስታመም በላይ የሰላም እጦት ፈተና ኾኖባቸዋል፡፡ “የሰላሙ እጦቱ ወጥተን እንዳንገባ አድርጎናል፤ ችግር እየገጠመን ነው ያለው፡፡ አርሶ አደሮች ነን እኛ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ እኛ እንዴት እንደምንኾን ግራ ግብት ብሎን ነው ያለነው፤ ገበያ ውለን ለመግባት አልቻልንም፡፡ የታመሙ ሰዎችን ወደ ሐኪም ቤት መውሰድ አልቻልንም፡፡ አርሶ አደሮች እየተጨናነቅን ነው፡፡ ችግሩ እንዴት እንደተፈጠረ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ችግሩ ግን እኛን ግራ አጋብቶናል” ነው ያሉት፡፡

ብዙዎች ባልፈጠሩት ችግር መከራ ይቀበላሉ፡፡ ያልተገባ ዋጋ ይከፍላሉ፡፡ በቀያቸው ሰላም ወጥቶ ለመግባት ይቸገራሉ፡፡ ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸውን ያልጠቀስነው የጤና ባለሙያ እንደገለጹልን በፀጥታው ችግር ምክንያት የትራንስፖርት መስተጓጎል በመፈጠሩ የመድኃኒት እጥረት ነው፡፡ የጤና ባለሙያው “መሠረታዊ የመድኃኒት እጥት አለ፡፡ በተለይ ለወላዶች፣ ተመላላሽ ታካሚዎች ለኾኑ ግፊት፣ ስኳር፣ የልብ ሕመም ላለባቸው ወገኖች የመድኃኒት እጥረት አለ” ብለዋል፡፡

“ታካሚዎች ወደ ሕክምና ሲመጡ የመጀመሪያው ሃሳባቸው ተቋማት ክፍት ኾነው እናገኛቸዋለን ወይስ አናገኛቸውም? የሚል ነው፡፡ ተቋማት ክፍት ኾነው ሲያገኟቸው በጣም ደስተኞች ናቸው፡፡ እኛም ከወቅታዊ ሁኔታው ጋር ተያይዞ የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እንዳለ እና በሚያገኙት አማራጭ ሁሉ መድኃኒት እንዲገዙ እንመክራቸዋለን” ነው ያሉት፡፡

የጤና ባለሙያው ሕሙማን እየደረሰባቸው ስላለው እንግልት እና ያልተገባ ወጪ ሲናገሩ “ታካሚዎች በመድኃኒት እጥረት ምክንያት ላልተገባ ወጪ እየተዳረጉ ነው ብለዋል፡፡ ነጋዴዎች ይሄን አጋጣሚ መጠቀም ይፈልጋሉ፡፡ በሰላም ጊዜ የሚሸጥ መድኃኒት እና በችግር ጊዜ የሚሸጥ መድኃኒት አንድ አይደለም፡፡ የተቸገሩ ሰዎች መድኃኒት እየገዙ ያሉት ከእጥፍ በላይ ነው፡፡ ሰዎች ሕይዎታቸውን ለመታደግ ከአቅም በላይ መድኃኒት እየገዙ ይወስዳሉ፡፡ ሕዝቡ በጣም እየተቸገረ ነው” ብለዋል፡፡

የጤና ባለሙያው ሰላም ሲኖር ሰው ጤንነቱን መጠበቅ ይችላል፤ የጤና ተቋማትም በነጻነት አገልግሎት ይሰጣሉ ነው ያሉት፡፡ የጤና ባለሙያዎችም በተረጋጋ መንፈስ ማከም የሚችሉት ሰላም ሲኖር ነው ብለዋል፡፡ የጦርነት የመጨረሻ ውጤት በምጣኔ ሃብት ላይ ብቻ ሳይኾን በጤና ላይም ታላቅ ጠባሳ ጥሎ ነው የሚያልፈው ነው ያሉት፡፡

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያዎች አቅርቦት ሥርጭት እና ክትትል ዳይሬክተር ዘለቀ አበጀ በክልሉ የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በመድኃኒት አቅርቦት እና ሥርጭት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ገልጸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ መድኃኒቶች ከአዲስ አበባ እንደሚመጡ የተናገሩት ዳይሬክተሩ በመንገዶች መዘጋጋት ምክንያት ወደ ክልሉ የሚገባው መድኃኒት በወቅቱ መግባት አለመቻሉን ተናግዋል፡፡

መድኃኒቶች ባሕር ዳር እና ጎንደር ላይ ከሚገኙ አቅራቢ አገልግሎቶች ወደተለያዩ ተቋማት በወቅቱ መድረስ እንዳይችሉ እንቅፋት መፈጠሩንም አመላክተዋል። የክልሉ ጤና ቢሮ በተለይም ተጀምረው የማይቋረጡ መድኃኒቶች ወደ ተቋማት እንዲገቡ ጥረት እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ መድኃኒቶች ወደ ክልሉ በካርጎ እንዲገቡ፣ መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት መድኃኒቶችን ለማስገባት የተሸክርካሪ ድጋፍ እንዲያደርጉ እና በዚያ አማካኝነት መድኃኒት እንዲገባ እየተደረገ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡ ችግሮችን ለመፍታት ከአጋር አካላት ጋር በመኾን ርብርብ እየተደገ ነው ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ጤናን ከፖለቲካ ነጥሎ በመለየት ዜጎች መድኃኒት እንዲያገኙ የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል፡፡ በመንግሥት ተቋማት እና በግል ተቋማት ላይ የዋጋ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችልም አንስተዋል። ይሕም የሕዝቡን የመግዛት አቅም እንደሚፈትን ጠቁመዋል። መፍትሔው መድኃኒቶች በመንግሥት ተቋማት ውስጥ በበቂ መጠን እንዲገኙ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ዘለቀ ተገልጋዮች ወደ ግል ተቋማት እየሄዱ በኢኮኖሚ እንዳይፈተኑ መድኃኒቶችን በመንግሥት ተቋማት እንዲያገኙ የማመቻቸት ሥራ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ በመንግሥት ተቋማት መድኃኒቶች ሲገኙ የተገልጋዮችን እንግልት እና ያለአግባብ ወጪ ማዳን ይቻላል ነው ያሉት፡፡ መድኃኒቶችን በጤና ተቋማት በተሟላ መንገድ ለማድረስ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በፀጥታ ችግር ምክንያት የሚፈጠረው የመድኃኒት አቅርቦት ችግር የሚጎዳው ሕዝብን መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ሕዝብን ማገልገል የሁሉም ኀላፊነት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ያለ ጤና ምንም ዓይነት ነገር ማድረግ እንደማይቻል በመረዳት የመድኃኒት አቅርቦት በበቂ ሁኔታ ተደራሽ እንዲኾን ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ እናቶችን፣ ሕጻናትን እና አባቶችን ለማትረፍ ከሁሉም ድጋፍ ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡ በመድኃኒት እጥረት ምክንያት ሊመጣ የሚችለውን ተጽዕኖ ግምት ውስጥ በማስገባት መድኃኒት በተገቢው መንገድ እንዲቀርብ ኅብረተሰቡ ሰላሙን በመጠበቅ ድጋፍ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል፡፡ መድኃኒት ከአዲስ አበባ ወደ ክልሉ፣ በክልሉም ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እንዲዳረስ መደጋገፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየከተማዋን የመንገድ ችግር ለመቅረፍ እየሠራ መኾኑን የደሴ ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።
Next articleከ800 በላይ በሚኾኑ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የተሳታፊ ልየታ ሥራ ማጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።