
ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በ2016 በጀት ዓመት በከተማ አሥተዳደሩ የተሠሩ ሥራዎችን ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል፡፡ ከንቲባው እንዳሉት ከተማ አሥተዳደሩ ወደ ልማት ከመግባቱ በፊት የሕዝብ ፍላጎትን መሠረት ያደረጉ የልማት ሥራዎችን የመለየት ሥራ ተሠርቷል። በተለይም ደግሞ የከተማዋ ዋነኛ ችግር የኾነውን መንገድ ለመገንባት እና ተጨማሪ ሃብት መፍጠር የሚችሉ ማሽነሪዎችን ግዥ ጭምር መፈጸም ተችሏል።
በከተማ አሥተዳደሩ ለሚገነቡ መሠረተ ልማቶች ለተነሱ ዜጎች ቦታ በማመቻቸት ማኅበረሰቡ በፈቃዱ እንዲነሳ ተደርጓል። ማኅበረሰቡ የልማቱ አጋዥም እንዲኾን ተደርጓል ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው። የከተማዋን የመንገድ ችግር ለመፍታት በበጀት ዓመቱ ከ15 ኪሎ ሜትር በላይ የሚኾኑ 10 የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክቶች እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። ከእነዚህ ውስጥ ትርፍ ሰዓት በመሥራት ጭምር አብዛኛዎቹ ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በማኅበረሰቡ ተሳትፎ መንገድ እና ቢሮዎችን መገንባት መቻሉንም ነው የጠቀሱት። የከንቲባ ችሎት በማስጀመር ማኅበረሰቡ ፊት ለፊት ለከንቲባው ችግሮችን እንዲያቀርብ ተደርጓል። በዚህም ለ12 ዓመት ፍጻሜ ሳያገኙ ተደብቀው የቆዩ ጉዳዮች መፍትሔ ማግኘታቸውን በማሳያነት አንስተዋል።
በከተማው የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ማኅበረሰቡ ሰላሙን እንዲያጸና እና የልማት አጋዥነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!