
ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል የስሜን ጎጃም ዞን የሲቭል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት መምሪያ “አገልጋይነት እና ሥልጡን ሲቪል ሰርቪስን ለመገንባት የመንግሥት ሠራተኛው ሚና” በሚል ርእሰ ጉዳይ ከዞኑ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ከተውጣጡ ሠራተኞች ጋር በባሕር ዳር ከተማ የትውውቅ ውይይት አድርጓል።
በውይይት መድረኩ ላይ ከንግድ እና ገበያ ልማት የተገኙት ባለሙያ ፋሲካ ላቀ እንዳሉት የትውውቅ ውይይቱ ሠራተኛው ተቀናጅቶ በመሥራት የአገልግሎት ፈላጊውን ማኅበረሰብ ጥያቄ በአግባቡ እንዲመልስ ያደርገዋል ብለዋል። ሥራ በቅንጅት ሲተገበር ደግሞ ግልጽ፣ ፍትሐዊ እና ቅልጥፍና ይኖረዋል ነው ያሉት። ወይዘሮ ፋሲካ ወቅቱ የቴክኖሎጂ በመኾኑ በተለይ የንግዱን ማኅበረሰብ ባለበት አካባቢ ኾኖ አገልግሎት ለመስጠት ስለሚያስችል ዞኑ ዘመናዊ አሠራርን እንዲያጎለብትም ጠቁመዋል።
በዞኑ የሲቪል ሰርቪስ ባለሙያ አበባው አበበ የሠለጠነ እና ሥልጡን ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት የሠራተኛውን አቅም በማጎልበት ጥራቱን የጠበቀ፣ ቀልጣፋ እና ከሙስና የጸዳ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል። ተቋማትን ከሰው ኃይል በተጨማሪ በቁሳቁስም በማሟላት የተሻለ ሥራ መሥራት እንደሚገባም በውይይቱ ላይ አብዛኛው ተወያይ ያንጸባረቀው ሃሳብ እንደኾነ አቶ አበባው ጠቁመዋል።
የዞኑ ሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት መምሪያ ኀላፊ ምህረት ይመኑ በዞኑ የሚገኙ ተቋማት እና የሰው ሃብቱ በአደረጃጀቱ ጠንካራ ፣ በሰው ኃይሉ የተሟላ፣ ተጠያቂ፣ ሕጋዊ አሠራርን ያከበረ እና በዘመናዊ ቴክኖሎጅ የተደራጀ ሲቪል ሰርቪስ በመገንባት ለሀገራዊ ብልጽግና መረባረብ የሚገባው ወቅት አሁን ነው ብለዋል።
መምሪያ ኀላፊው አያይዘውም “የእኛ ዘመን ቁርጠኝነት እንደ አባቶቻችን የሕይዎት መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ሳይኾን በንፁህ ሕሊና፣ በሀገር ፍቅር ስሜት፣ ለትውልድ ታማኝ በመኾን ሕዝብን ማገልገል በመኾኑ ለተግባራዊነቱም እየተጋን እንገኛለን” ነው ያሉት። በዞኑ አመራሩ ከአገልጋይነት ጋር ተያይዞ ኀላፊነቱን እየተወጣ ነው ያሉት ኀላፊው ተገልጋዩም ማሟላት የሚገባውን ቅድመ ኹኔታ በማሟላት የተሻለ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችለው አሠራርም እየተዘረጋ ነው ብለዋል።
የስሜን ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሰፋ ጥላሁን በዞኑ ሁሉም ሥራ የሚከናወነው በመመሪያ እና በሕግ በመኾኑ ጥሩ ሲቪል ሰርቪስ እየተገነባ ነው ሲሉ አብራርተዋል። ዋና አሥተዳዳሪው በዞኑ የተከሰተው የጸጥታ ችግር ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ ማድረጉን አስታውሰው፤ የጸጥታ ችግር ኑሮ እንኳ ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። የማኅበረሰቡን ጥያቄ ለመመለስም ሠራተኛው ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ መግባት እንዳለበትም ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!