መንግሥት የሀገሪቷ ወቅታዊ ፈተናዎች የኾኑትን ሥራ አጥነት እና የኑሮ ውድነት ለመቀነስ በትኩረት እንደሚሠራ ተገለጸ።

12

ደሴ: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የደሴ ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ፣ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ በአምስቱም ክፍለ ከተሞች ከሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር ተወያይቷል። የደሴ ከተማ አሥተዳደር የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ አዝመራ ማስረሻ ለውይይቱ መነሻ የሚኾን ጽሑፍ አቅርበዋል።

በየደረጃው በተደረጉ የሕዝብ ውይይቶች ሕዝቡ ለሰላሙ ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ልማት ፈላጊ እና የመልካም አሥተዳደር ችግሮች እንዲፈቱለት ያለመታከት በሰላማዊ መንገዶች የሚታገል ነው ብለዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ከተማ አሥተዳደሩ ከሕዝቡ ጋር በጋራ በመኾን በከተማዋ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እየገነባ በመኾኑ ምስጋናቸውን አቅርበው፤ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ከኑሮ ውድነት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ በክልሉ እና በፌዴራል መንግሥት ምላሽ ሊሰጣቸው ይገባልም ነው ያሉት። በትምህርት ቤቶችም የግብረ ገብ ትምህርቱን በማጠናከር የተሻለ ትውልድ እንዲፈጠር በመሥራት የበለጸገች ኢትዮጵያን መገንባት አለብን ብለዋል።

የደሴ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ከተማዋ በአንጻራዊነት ሰላሟ ተጠብቆ እንድትቀጥል እና የተጀመሩ የመሠረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የመንግሥት ሠራተኞች የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።

በቀጣይም በሰላም፣ በልማት እና በመልካም አሥተዳደር ሥራዎች አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች የሚጠበቅባቸውን ኀላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ሥራ አጥነት እና የኑሮ ውድነት የወቅቱ የሀገራችን ፈተናዎች በመኾናቸው ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን ብለዋል። በዚህም ክልላችን የሚያመነጨውን ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ ይገባል ነው ያሉት።

ትምህርት እና ጤና ትውልድ የምንገነባባቸው ማኅበራዊ መስኮች በመኾናቸው የትምህርት ጥራት እና የጤና ተቋማት ፍትሃዊነት ላይ አበክረን እንሠራለን ብለዋል።

ዘጋቢ፡- አንተነህ ፀጋዬ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየከተሞችን ልማት ዘላቂነት ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡ ለሰላም ዘብ እንዲቆም ተጠየቀ።
Next article“የእኛ ዘመን ቁርጠኝነት እንደ አባቶቻችን የሕይዎት መስዋዕትነትን የሚጠይቅ ሳይኾን በሀገር ፍቅር ስሜት ሕዝብን ማገልገል ነው” የስሜን ጎጃም ዞን ሲቪል ሰርቪስ መምሪያ