
ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በክልሉ የተከሰተው የጸጥታ ችግር የከተሞችን የመልማት አቅም መግታቱን የጎንደር እና ደብረ ታቦር ከተማ ከንቲባዎች ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። ጎንደር ከ200 ዓመታት በላይ የሀገሪቱ መናገሻ የነበረች፣ 17 ነገሥታት የነገሱባት፣ አሁንም ድረስ ታሪካዊነታቸውን ጠብቀው የሚገኙ በየዘመናቱ በነገሱ ነገሥታት የተገነቡ አብያተ መንግሥታ መገኛ ናት።
ይሁን እንጅ ባለፉት ዓመታት በአካባቢው በተከሰቱ ግጭቶች እና የተለያዩ ምክንያቶች የከተማዋን ታሪክ እና እድሜ የሚመጥን ልማት ርቋት መቆየቱን የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል። በ2016 በጀት ዓመት ችግሮችን በመፍታት ከተማዋን የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። በከተማዋ በተለያዩ የዓለም ሀገራት እየተተገበረ የሚገኘውን “ስማርት ሲቲ” ጽንሰ ሃሳብ ለመተግበር ስትራቴጅክ እቅድ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል ብለዋል።
ለስማርት ሲቲ ትግበራ አመች የኾኑ እንደ ሲቹዌሽን ሩም፣ የካዳስተር ቦታዎችን ማዘጋጀት እና የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችን የማልማት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት። ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት 14 በሚኾኑ ጉዳዮች ላይ የሚታዩ ችግሮችን የመለየት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። ከዚህ ውስጥ የገቢ አቅም ጥናት ተጠንቶ መጠናቀቁን በማሳያነት አንስተዋል።
ባለፉት ዓመታት በከተማዋ ለመሥራት ከታቀዱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል 18 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ግንባታ ተጠናቅቋል ብለዋል። በቀጣይም ፕሮጀክቶቹን ወደ አስፋልት ለማሳደግ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። በ600 ሚሊዮን ብር ከተማዋን የሚመጥን የዘመናዊ ቄራ ግንባታ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ ከተለዩት አምስት የኢንዱስትሪ መንደሮች ውስጥ በአምስተኛው የኢንዱስትሪ ፓርክ በ32 ሚሊዮን ብር የመንገድ እና የድልድይ ግንባታ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። ባለፉት ስምንት ወራት ከ83 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 206 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል። ከዚህ ውስት ለ47 ባለሃብቶች 42 ሄክታር መሬት ተላልፏል፤ 9 የሚኾኑትም ወደ ግንባታ ገብተዋል።
እስከ አሁን ለ20 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል መፈጠሩንም አንስተዋል። ከዚህ ውስጥ 8 ሺህ በላይ የሚኾኑት በቋሚነት ሥራ የተፈጠረላቸው ናቸው። የከንቲባ ችሎት በማካሄድ በከተማዋ የነበረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር መፍታት መቻሉንም ገልጸዋል። የደብረ ታቦር ከተማ ከንቲባ ደሴ መኮንን እንዳሉት ደግሞ ደብረ ታቦር እንደ ጥንታዊነቷ እና የመጀመሪያው የጋፋት ኢንዱስትሪ መንደር ጠንሳሽነቷ እድሜዋን የሚመጥን ልማት ናፍቋት ቆይቷል።
በበጀት ዓመቱ በከተማ አሥተዳደሩ ሰላሙን ከማረጋጋት ባለፈ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲጠናከር ተደርጓል። ወጣቶች በእንስሳት ሃብት ልማት ሥራ እንዲሰማሩ ተደርጓል። በከተማዋ የሚታየውን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት የሰብስቴሽን ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል። አሁን ላይ ከ50 በመቶ በላይ መጠናቀቁንም ከንቲባው ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት በከተማው በሕገ ወጥ መንገድ ተይዞ የነበረውን መሬት የማስመለስ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ነው የገለጹት። በጸጥታ ችግር ምክንያት ቆመው የነበሩ የግል እና የመንግሥት የኮንስትራክሽን ሥራዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉንም አንስተዋል። በከተማዋ ማልማት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች የመስሪያ ቦታ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል። መሪዎቹ የከተሞቹን ልማት በታቀደላቸው ልክ ለመፈጸም እንዲቻል ማኅበረሰቡ ለሰላም ዘብ እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!