“ከሰሞኑ በትግራይ ክልል በኩል በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታየው አዝማሚያ ተገቢነት የሌለው ብቻ ሳይኾን የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ ነው” ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)

173

ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸውም ከሰሞኑ በትግራይ ክልል በኩል የተፈጸመውን ትንኮሳ በተመለከተ አንስተዋል፡፡

መንግሥት ስምምነቶቹ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት እንዲተገበሩ ቁርጠኛ መኾኑን ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ከሰላም ስምምነቱ የተሻገረ ሥራ መሥራቱንም ተናግረዋል፡፡ ሰላም እንዲጸና ሁሉንም ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡ ከሰሞኑ በትግራይ ክልል በኩል በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታየው አዝማሚያ ተገቢነት የሌለው ብቻ ሳይኾን የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ ነው ብለዋል፡፡

የሚነሱ ጥያቄዎችን እና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት እና በድርድር ከመፍታት ይልቅ ወሰንን በኃይል እናስከብራለን የሚል አካሄድ ካለፈው ስሕተት አለመማርን ያመለክታል ነው ያሉት፡፡ ሰላሙን እያጸና የሚገኘውን የትግራይ ሕዝብ ለሌላ ዙር ስቃይ እና እንግልት የሚዳርግ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
በክልሉ እና በአጎራባች አካባቢዎች የተፈጠረውን አንጻራዊ ሰላም የሚያደበዝዝ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በኋላ በተጀመረው መንገድ በተቀመጠው አቅጣጫ ብቻ ችግሮች እንዲፈቱ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

የፌዴራል መንግሥት የማንነት እና የወሰን ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ ብቻ እንዲፈታ ግልጽ አቅጣጫ ማስቀመጡንም አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ ለጊዜው ትርፍ የሚያስገኝ ቢመስልም ዘላቂነት አይኖረው ነው ያሉት፡፡ ከፌዴራል እና ከሁለቱም ክልሎች የተውጣጣው ዐቢይ ኮሚቴ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል፡፡

የወሰን እና የማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች ጉዳዩ እልባት እስኪያገኝ ድረስ እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡ ተፈናቃዮችም ወደ ቀያቸው መመለስ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ በሁለቱ ክልሎች ሰላም እና መረጋጋት እንዳይመጣ የጽንፈኛ ኃይሎች የዘረጉትን ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውር ለመቆጣጠር ሁለቱም ክልሎች መቆጣጠር አለባቸው ነው ያሉት፡፡

ባለፉት ወራት መንግሥት ታላላቅ ውይይቶችን ማድረጉንም ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር መወያያታቸውንም አንስተዋል፡፡ ውይይቶቹም ስኬታማ እንደነበሩ ነው የተናገሩት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በአማራ ክልል እየተወሰደ ባለው ውጤታማ እርምጃ ክልሉ ወደ ተሻለ ሰላም እና መረጋጋት መጥቷል” ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)
Next articleዘላቂ እና አስተማማኝ ሰላምን ለማስፈን ከመንግሥት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሠሩ የሰከላ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።