“በአማራ ክልል እየተወሰደ ባለው ውጤታማ እርምጃ ክልሉ ወደ ተሻለ ሰላም እና መረጋጋት መጥቷል” ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)

75

ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫቸውም መንግሥት ችግሮችን በሰላማዊ አማራጮች ለመፍታት ጥረት እያደረገ የቆየ እና ሁልጊዜም ለሰላም በሩ ክፍት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ይህ አልሳካ ሲል የሀገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ሕግ የማስከበር ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ በተሠራው ሥራ አብዛኛዎቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም እና መረጋጋት ላይ መኾናቸውን አመላክተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በአማራ ክልል የተጀመረው የሕግ ማስከበር ሥራ ውጤታማነቱን ጠብቆ እንደቀጠለ ነው ብለዋል፡፡ በተወሰዱ እርምጃዎች ክልሉ ከሞላ ጎደል ወደ ተሟላ ሰላም እና መረጋጋት ለመምጣት የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሮለታል ነው ያሉት፡፡ የፖለቲካ፣ የአሥተዳደር እና የፀጥታ መዋቅሩን የማጥራት፣ መልሶ የማደራጀት አቅሙን የመገንባት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡

የክልሉ የፀጥታ ኃይል ተገቢውን ሥልጠና በመውሰድ ራሱን በማደረጀት በየቀበሌው እና በየወረዳው የአካባቢውን ሰላም በመጠቀብ መረጋጋት እንዲፈጠር እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ በልዩ ልዩ አሳሳች መረጃዎች ከጽንፈኛው እና ዘራፊው ኃይል ጎን ተሰልፎ የነበረው ኃይል ከ12 ሺህ በላይ የሚኾነው የቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ተሐድሶ በመውሰድ ከኅብረሰቡ ጋር ለመኖር ተቀላቅሏል ነው ያሉት፡፡

በልዩ ልዩ ምክንያት አኩርፈው እና ተበትነው የነበሩ ከ10 ሺህ ያላነሱ የቀድሞ ልዩ ኃይል አባላት በተደረገላቸው ጥሪ መሠረት በተሐድሶ ሥልጠናዎች አልፈው ክልሉን ከጥፋት ኃይሎች ለመታደግ የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ ነው ያሉት፡፡ የክልሉ መሪዎች የክልሉን ሕዝብ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያስችሉ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ሥራዎችን እያፋጠኑ፣ በሌላ በኩል ሰላምን ለማጽናት ርብርብ እያደረጉ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

“በአማራ ክልል እየተወሰደ ባለው ውጤታማ እርምጃ ክልሉ ወደ ተሻለ ሰላም እና መረጋጋት መጥቷል” ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡ የአማራ ክልል የጥፋት ፕሮፖጋንዳ ደጋሾች እንደሚያራግቡት አለመኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያ እና መሬት ላይ ያለው እውነታ የተለያዬ ነው ብለዋል፡፡

የጽንፈኛ እና ዘራፊ ቡድኑ የሚወሰድበትን እርምጃ መቋቋም ተስኖት እና ተዳክሞ ራሱን ለማቆየት ሲል በዘረፋ ተግባር ላይ ተሰማርቷል ነው ያሉት፡፡ ጊዜ እየጠበቀ መዝረፍ እና ማውደሙን ሥራዬ ብሎ ቀጥሎበታል ብለዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች አርሶ አደሮች ማዳበሪያ እንዳይደርሳቸው እንቅፋት እየኾነ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡ ከተስፋ መቁረጥ እና ከዓላማ ቢስነት የሚመነጨውን እኩይ ድርጊቱን ለመግታት የፀጥታ ኃይሎች፣ የክልሉ መንግሥት እና የአማራ ሕዝብ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል ነው ያሉት፡፡ በአጭር ጊዜ ተልዕኳቸውን እንደሚያጠናቅቁም አመላክተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል እየተወሰደ ባለው እርምጃም ቀያቸውን ለቀው በአማራ ክልል የተጠለሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡ በክልሎች የተቀናጀ ጥረት የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ ተፈናቃዮችን የመመለስ ጉዳይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየማኅበራዊ ሚዲያ አልጎሪዝም (ስልተ ቀመር)
Next article“ከሰሞኑ በትግራይ ክልል በኩል በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚታየው አዝማሚያ ተገቢነት የሌለው ብቻ ሳይኾን የፕሪቶሪያውን ስምምነት የሚጥስ ነው” ለገሰ ቱሉ (ዶ.ር)