
ባሕር ዳር: መጋቢት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አልጎሪዝም የሚለው ቃል በኮምፒውተሩ ዓለም በጣም የተለመደ ቃል ነው፡፡ ከዘርፉ ባለሙያዎች ውጨ ያሉ ሰዎችም ቃሉን አልፎ አልፎ ሲጠቀሙት እናስተውላለን፡፡ አልጎሪዝም ታዲያ ምንድን ነው? በአማርኛ መግለጽስ እንችላለን?
እነዚህ እንደመንደርደሪያ ያስቀመጥናቸው ጥያቄዎች በዚህ ጽሑፍ ዝርዘር ውስጥ ያለውን ጉዳይ ለመረዳት መሠረታዊ በመኾናቸው በቀላል ገለጻ መልሰናቸው እናልፋለን፡፡
በአማርኛ አልጎሪዝም የሚለውን ቃል “ስልተ ቀመር” ወይም የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን ለማልማት የምንጠቀምበት የአሠራር ቅደም ተከተልን የሚያሳይ መመሪያ በሚል ልንገልጸው እንችላለን፡፡ አንድን ችግር ለመፍታት የሚያስችል መተግበሪያን ለመሥራት ወይም ውስብስብ ስሌቶችን ለማስላት የምንከተለው የአሠራር ቅደም ተከተል እንደማለት ነው፡፡ አንድን ተግባር በአፈጻጸም ሂደቱ ለመተግበር የሚያስችል መሪ ነው፡፡
አልጎሪዝም በሁሉም የመረጃ ቴክኖሎጂ ዘርፎች በስፋት ጥቅም ላይ የሚውል ነው። በሒሳብ፣ በኮምፒውተር ሳይንስ እና ኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ዘርፎች አልጎሪዝም ማለት አስቸጋሪ ጥያቄዎችን የመፍቻ መንገድ ነው። አልጎሪዝምን ለተለያዩ ተግባራት መጠቀም እንችላለን ቀለል ያሉ የቁጥሮች ስብስብን ከማደራጀት ጀምሮ በማኅበራዊ ሚዲያ ለተጠቃሚዎች ይዘትን እንዲከታተሉ እስከመጋበዝ የሚደርሱ ሥራዎችን ይሠራሉ።
በዋናነት አልጎሪዝሞች አንድን ተግባር ለመፈጸም የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን (Inputs) በመለየት እና ተግባሩን ለማከናውን የምንከተለውን መመሪያ በማስቀመጥ የሚተገበሩ ናቸው። አልጎሪዝሞች የተቀመጠን የመመሪያዎች ስብስብ ወይም ሕጎች በመጠቀም ተግባራትን ለመከውን እና ችግሮችን ለመፍታት ያገለግላሉ። በተለያየ መንገድ ሊገለጹ ይችላሉ። በመደበኛ ቋንቋ፣ የፕሮግራሚንግ ቋንቋዎች፣ በኮዶች፣ በክዋኔ ዑደት ማሳያ እና በክዋኔ መከታተያ ሰንጠረዥ (Control Table) ሊቀርብ ይችላል።
ብዙ ዓይነት አልጎሪዝዎችን በተለያየ አጋጣሚ የማስተዋል እድል ገጥሞን ሊኾን ይችላል። የትኛውም አልጎሪዝም ግቡ የታለመለትን ተግባር መከወን እና ችግሮችን መፍታት ነው። የመረጃ ማሰሻ አልጎሪዝም (Search Engine Algorithm)፣ የመቆለፊያ አልጎሪዝሞች (Encryption Algorithm)፣ ተለዋዋጭ የፕሮግራሚንግ አልጎሪዝም (Dynamic Programming Algorithm)፣ በግመታ ችግሮችን ለመፍታት የሚያገለግል አልጎሪዝም (Brute-force Algorithm)፣ መረጃን ወደ አንድ ወጥ ቅርጽ የሚቀይርልን አልጎሪዝም (Hashing Algorithm) እና ሌሎችም የአልጎሪዝም ዓይነቶች አሉ።
አልጎሪዝሞች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያላቸው አገልግሎት ከፍተኛ ነው። በተለይ ደግሞ ለማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች ትልቅ የገቢ ምንጭ ኾነዋል። ኩባንያዎቹ ተጠቃሚዎቻቸውን ለማሳደግ እና ለመቆጣጠር የሚያገለግላቸው አሠራር በመፍጠራቸው ያልተገባ ወይም የሥነ ልቦና ጫና የሚፈጥር ሥርዓት ፈጥረዋል የሚል ትችት እየተሰነዘረባቸው ይገኛል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ኔት ፍሌክስ የሠራው “ዘ ሶሻል ዳይለማ” የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም የኩባንያዎቹን ጫና የሚያሳይ ነው።
በዚህ ዘጋቢ ፊልም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚው ለሽያጭ የቀረበ ሸቀጥ እንደተደረገ ያስረዳል። ኩባንያዎቹ ተጠቃሚዎች ባላቸው አጠቃቀም ልክ ለትላልቅ የንግድ ማስታወቂያዎች ተጋላጭ እንዲኾኑ ያደርጋል። ተጠቃሚውን ለንግድ ተቋማት የሚሸጡ ኩባንያዎች ፍላጎታቸው እንዲሟላ የሚረዳቸው ደግሞ የተጠቃሚዎቻቸውን ፍላጐት የሚለይ አልጎሪዝም ነው፡፡
ቲክቶክ የሚጠቀመው አልጎሪዝም የእኛን አዕምሮ በጣም የተረዳ የሚመስል ነው። ባለን አካባቢያዊ ሁኔታ፣ በምንጠቀመው የስልክ ዓይነት እና የቋንቋ መቼት (setting) ልክ የተለያዩ ይዘቶችን እንድንከታልል ተጽዕኖ የሚፈጥር አልጎሪዝም አለው። ሌላኛው የማኅበራዊ ሚዲያ አማራጭ ፌስቡክ የሚጠቀመው አልጎሪዝምም የሚኖረንን ግንኙነት እንደመነሻ በመውሰድ ምን ዓይነት ይዘት ማየት እንዳለብን ይወስንልናል።
ዩቲዩብም እንዲህ ዓይነት አልጎሪዝሞችን ይጠቀማል። በዚህ ፕላትፎርም ይዘቶችን ከሚከታተሉ ሰዎች ውስጥ 70 በመቶ የሚኾኑት የዩቲዩብ አልጎሪዝም የሚያቀርብላቸውን ይዘት የሚከታተሉ ናቸው። አልጎሪዝሞች ተጠቃሚዎች ላይ በሚፈጥሩት ተጽዕኖ ምክንያት ሰዎች በውል ባልተረዱት ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል የሚል ወቀሳ ይደርስበታል።
“በተፈጠረልህ ዓለም ውስጥ እንዳለህ ሳታውቅ እንዴት ከዚህ መንቃት ትችላለህ?” በማለት የኔት ፍሌክሱ ዘጋቢ ፊልም በተፈጠረ ዓለም ውስጥ እንዳለን እና ከዚህ ዓለም ለመንቃት መጀመሪያ ያለንበትን ዓለም መረዳት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል፡፡
ምንጮቻችን፦ https://www.techtarget.com/whatis/definition/social-media
https://quickframe.com/…/how-do-social-media…/
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!